ትራምፕ ከዚህ ምርጫ በኋላ "በየአራት አመቱ አትመርጡም" ሲሉ ለክርስቲያኖች መናገራቸው አነጋገረ
በዲሞክራት ተቀናቃኞቻቸው የዲሞክራሲ ጸር ናቸው የሚል ክስ የሚቀርብባቸው ትራምፕ፣ በዚህ ንግግራቸው ምን ለማለት እንደፈለጉ ግልጽ አይደለም
ትራምፕ በናሽናል ሪፍልስ ማህበር ስብሰባ ወቅት ባደረጉት ንግግር ከሁለት ዙር የስልጣን ዘመን በላይ የማገልገል ፍላጎት እንዳላቸው አመላክተዋል
የሪፐብሊካኑ ፕሬዝደንታዊ እጩ ዶናልድ ትራምፕ ለክርስቲያኖች በዚህ ምርጫ ከመረጧቸው "በየአራት አመቱ መምረጥ አይጠበቅባችሁም" ማለታቸው አነጋጋሪ ሆኗል።
ትራምፕ ባለፈው አርብ እለት በህዳሩ ምርጫ ከመረጧቸው "በየአራት አመቱ መምረጥ አይጠበቅባችሁም። ችግሩን እንፈታዋለን፤ ድጋሚ አትመርጡም" ሲሉ ለክርስቲያኖች ተናግረዋል።
በዲሞክራት ተቀናቃኞቻቸው የዲሞክራሲ ጸር ናቸው የሚል ክስ የሚቀርብባቸው ትራምፕ፣ በዚህ ንግግራቸው ምን ለማለት እንደፈለጉ ግልጽ አይደለም።
ትራምፕ ይህን ያሉት 'ተርኒንግ ፖይነት አክሽን' የተባለው ወግአጥባቂ ቡድን ፍሎሪዳ ውስጥ ባዘጋጀው ፕሮግራም ላይ ነው።
ትራምፕ "ክርሲያኖች ውጡና ምረጡ፣ ጊዜ አትፍጁ። ከዚህ በኋላ አትመርጡም። ከዚህ በኋላ እናስተካክለዋለን፣ ጥሩ ይሆናል። ከዚህ በኋላ በየአራት አመቱ አትመርጡም፣ የእኔ ውድ ክርስቲያኖች" ብለዋል።
ትራምፕ አክለውም "ክርስቲያን እወዳለሁ። ክርስቲያን ነኝ።" ሲሉ ተናግረዋል።
የትራምፕ ምርጫ ቅስቀሳ ቃል አቀባይ ስቴቨን ቸንግ የትራምፕን ንግግር እንዲያብራሩ ቢጠየቁም፣ በቀጥታ ምላሽ አልሰጡም።
ትራምፕ "እያወሩ ያሉት ሀገሪቱን አንድ ስለማድረግ ነው" ያሉት ቸንግ ለተፈጠረው ከፋፋይ የፖለቲካ ሁኔታ ከሁለት ሳምንት በፊት በትራምፕ ላይ የተቃጣውን የግድያ ሙከራ ተጠያቂ አድርገዋል። በትራምፕ ላይ የግድያ ሙከራ የፈጸመው የ2ዐቱ ወጣት አላማው ምን እንደሆነ መርማሪዎች እስካሁን ይፋ አላደረጉም።
ትራምፕ በታህሳስ ወር ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በመጭው ህዳር የሚካሄደውን ምርጫ የሚያሽንፉ ከሆነ ለአንድ ቀን ብቻ አምባገንን እንደሚሆኑ ተናግረው ነበር። ትራምፕ ለአንድ ቀን ብቻ አምባገንን እንደሚሆኑ የገለጹት ከሜክሲኮ ጋር ያለውን ድንበር ለመዘጋት ያላቸውን ፍላጎት ለማመላከት ነው።
ዲሞክራቶች ይህን የትራምፕ ንግግር በቀላሉ አላዩትም። ነገርግን ትራምፕ ከዚህ ወዲህ ንግግራቸው ቀልድ መሆኑን ገልጸዋል። ትራምፕ የመጭውን ምርጫ ካሸነፉ በስልጣን የሚቆዩት ለአራት አመት ብቻ ነው። በአሜሪካ ህገመንግስት መሰረት የፕሬዝደንቶች የስልጣን ዘመን በተከታታይ ወይም በተለያየ ጊዜ በሁለት ዙር የስልጣን ዘመን የተገደበ ነው።
ትራምፕ ባለፈው ግንቦት በናሽናል ሪፍልስ ማህበር ስብሰባ ወቅት ባደረጉት ንግግር ከሁለት ዙር የስልጣን ዘመን በላይ የማገልገል ፍላጎት እንዳላቸው አመላክተዋል። ትራምፕ ከሁለት ዙር የስልጣን ዘመን በላይ ያገለገሉት የዲሞክራቱ ፍለራንክሊን ዲ.ሩዝቬልት ብቻ እንደነበሩም ጠቅሰዋል። በአሜሪካ ፕሬዝደንቶች የስልጣን ዘመን ላይ ገደብ የተጣለው ከሩዝቬልት በኋላ ነው።