ትራምፕ ሁለተኛውን ዙር የምርጫ ክርክር ከካማላ ሃሪስ ጋር ለማድረግ ተስማሙ
በፎክስ ኒውስ አዘጋጅነት በሚካሄደው የምርጫ ክርክር ላይ ተመልካቾች እንዲታደሙ ተፈቅዷል
ሁለተኛው ዙር ክርክር የምርጫውን አሸናፊነት ይወስናሉ ከሚባሉ ግዛቶች መካከል አንዷ በሆነችው ፔንሴልቬንያ ይካሄዳል
የሪፐብሊካኑ እጩ ዶናልድ ትራምፕ ባይደንን ተክተው የዴሞክራት እጩ እንደሚሆኑ ከሚጠበቁት ካማላ ሃሪስ ጋር በሁለተኛው ምርጫ ክርክር ለመሳተፍ ተስማምተዋል፡፡
በአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የተካሄደው የመጀመርያ ዙር ክርክር የባይደንን የዴሞክራት እጩነት አስከፍሏል፡፡
በሲኤንኤን አዘጋጅነት ያልተመልካች በዝግ ስቱድዮ በተደረገው ክርክር ሀሳባቸውን በቅጡ መግለጽ ሲሳናቸው የታዩት ጆ ባይደን ከእጩነት እንዲነሱ ተቃውሞ በርትቶባቸው ከምርጫው እራሳቸውን ማግለላቸው የሚታወስ ነው፡፡
ለ90 ደቂቃ በተካሄደው ክርክር ዶናልድ ትራምፕ አንዳንድ ከእውነታነት ከራቁ ሃሳቦቻቸው ጭምር በባይደን ላይ ብልጫ እንደወሰዱ ብዙዎች ተስማምተዋል፡፡
በፈረንጆቹ መስከረም አራት ትራምፕ ከግድያ ሙከራ በተረፉበት የፔንሴልቬኒያ ግዛት ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ክርክር ከመጀመርያው ዙር ከተካሄደው ክርክር በተለየ ሁኔታ ተመልካቾች በስቱድዮ ውስጥ የሚታደሙ ይሆናል፡፡
ትራምፕ ክርክሩን አስመልክቶ ትሩዝ በተሰኘው የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ “ሁለተኛው ዙር ክርክር ከእንቅልፋሙ ጆ ባይደን ጋር ካደረኩት ክርክር እምብዛም የሚለይ አይደለም፤ ባይደን ከእኔ ጋር በእኩል መጋፈጥ አቅቶት በፓርቲው እንደተወገዘው ሁሉ ሀሪስም ተመሳሳይ እጣ ፈንታ ይገጥማታል” ብለዋል፡፡
በመጭው ነሀሴ 16 በይፋ የዴሞክራት እጩ እንደሚሆኑ የሚጠበቁት ካማላ ሃሪስ ስለ ክርክሩ ይፋዊ ምላሽ ባይሰጡም ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው ቃለ ምልልሶች ትራምፕን ፊት ለፊት ለመጋፈጥ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና በዶናልድ ትራምፕ መካከል በተደረገው የመጀመርያ ዙር የምርጫ ክርክር ወቅት የስደተኞች ጉዳይ ፣ የአሜሪካ ኢኮኖሚ ፣ የሁለቱ ፕሬዝዳንቶች የማስተዳደር አቅም ፣ የጋዛ እና የዩክሬን ጦርነት ጉዳዮች ዋነኛ መከራከሪያ እንደነበሩ የሚታወስ ነው።
ሃሪስ እና ትራምፕ በመስከረም ወር ያደርጉታል ተብሎ በሚጠበቀው ክርክር ላይ የሚነሱ ዋነኛ አጀንዳዎች ምን እንደሆኑ እስካሁን በይፋ ባይታወቅም ከዴሞክራቶች የእጩ ለውጥ ጋር በተያያዘ አዳዲስ የክርክር ሀሳቦች እንደሚካተቱ ይጠበቃል፡፡
ምንም እንኳን ትራምፕ በምርጫ ፉክክሩ ሃሪስ ከባይደን በተሻለ ቀላል ተፎካካሪ እንደሆኑ ቢናገሩም ሳምንቱን እየተለዋወጡ የመጡት አሀዛዊ መረጃዎች ካማላ ሃሪስ ከባይደን የተሻሉ ብርቱ ተፎካካሪ ሊሆኑ እንደሚችሉ አመላካች ስለመሆናቸው ተዘግቧል፡፡
ከአራት ሳምንታት በፊት ለመምረጥ በተመዘገቡ አሜሪካውያን ዘንድ በተወሰደ ድምጽ ትራምፕ ባይደንን በስምንት በመቶ ድምጽ እየመሯቸው ነበር፡፡
ካማላ ሃሪስ አዲሷ የዴሞክራ እጩ ሊሆኑ እንደሚችሉ ከተነገረ በኋላ ግን በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል ያለው የአሸናፊነት ግምት ልዩነት በሁለት በመቶ መጥበቡ ነው የተገለጸው።