ካማላ ሃሪስ ለምርጫ ቅስቀሳ የሚውል በአንድ ሳምንት ውስጥ 200 ሚሊየን ዶላር አሰባሰቡ
በርካታ የዴሞክራት ለጋሾች ከባይደን ከእጩነት ጋር በተያያዘ ለፓርቲው የሚያደርጉትን ድጋፍ አቋርጠው ነበር
የቅድመ ምርጫ የህዝብ አስተያየቶች ሃሪስ ከጆባይደን የተሻለ ተቀባይነት እንዳላቸው አመላክተዋል
አዲሷ የዴሞክራት እጩ እንደሚሆኑ የሚጠበቁት ካማላ ሃሪስ በአንድ ሳምንት ውስጥ 200 ሚሊየን ዶላር የምርጫ ቅስቀሳ ገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰባቸው ተነገረ፡፡
ከሳምንት በፊት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በዴሞክራት እጩነት እንደማይቀጥሉ ማሳወቃቸውን ተከትሎ ወደ ፊት የመጡት ምክትል ፕሬዝዳንቷ ካማላ ሃሪስ የፓርቲው ቀጣይ እጩ ለመሆን የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ አግኝተዋል፡፡
ይህን ተከትሎም በአንድ ሳምንት ውስጥ ካሰባሰቡት ገንዘብ ባለፈ 170 ሺህ በምርጫ ቅስቀሳው የሚያግዙ በጎ ፈቃደኞች መመዝገባቸውን የፕሬዝዳንቷ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን አስታውቋል፡፡
ተቀናቃኛቸው ዶንልድ ትራምፕ በሀምሌ ወር ሁለተኛው አጋማሽ 331 ሚሊየን ዶላር ማሰባሰብ የቻሉ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 284.9 በእጃቸው ላይ የሚገኝ ገንዘብ ነው፤ በተመሳሳይ ወቅት የጆ ባይደን የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ማሰባሰብ የቻለው 264 ሚሊየን ዶላር ነበር፡፡
ካማላ ሃሪስ አሰባሰቡት የተባለው ገንዘብ 66 በመቶ ከአዲስ ለጋሾች የተገኝ መሆኑ ሲገለጽ ይህም ሃሪስ ከባይደን የተሻለ ተቀባይት እንዳገኙ አመለካች ነው ተብሏል፡፡
በጆ ባይደን እና በትራምፕ መካከል ቀደም ብሎ በነበረው ፉክክር በቅድመ ምርጫ የህዝብ አስተያየቶች ትራምፕ ወሳኝ የሚባሉ የምርጫ ግዛቶችን ጨምሮ በመላው አሜሪካ በተመዘገቡ መራጭ ዜጎች ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት እና ለምርጫ አሸናፊነት የተሰጣቸው ግምት ከፈተኛ ነበር፡፡
ካማላ ሃሪስ አዲሷ የዴሞክራ እጩ ሊሆኑ እንደሚችሉ ከተነገረ በኋላ ግን በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል ያለው የአሸናፊነት ግምት ልዩነት በሁለት በመቶ ማጥበብ ችለዋል፡፡
ትራምፕ እና ሃሪስ የህዳር አምስቱን ምርጫ አሸናፊ ይወስናሉ በሚባሉ ወሳኝ ግዛቶች ኤመርሰን ኮሌጅ ፣ ሮይርስ እና ኒዮርክ ታይምስ ለየብቻ ባሰባሰቧቸው የህዝብ አሰተያየቶች፤ ጆርጂያ 48% ለ 46% ፣ ሚቺጋን 46% ለ 45% ፣ ፔንሴልቫኒያ 48% ለ 46 % ፣ አሪዞና 49% ለ 44% ዊስኮንሲን ላይ ደግሞ በእኩል 47 በመቶ ድምጽ የተቀራረበ የህዝብ ድጋፍ እንዳላቸው አመላክቷል፡፡
በአጠቃላይ ካማላ ሃሪስ ለምርጫ ከተመዘገቡ መራጮች ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት በ3 በመቶ ያደገ ሲሆን ከሶስት ሳምንታት በፊት በእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች በተወሰደ ድምጽ ትራምፕ ባይደንን በስምንት በመቶ ድምጽ እየመሯቸው እንደነበር ተገልጿል፡
ምንም እንኳን ትራምፕ በምርጫ ፉክክሩ ሃሪስ ከባይደን በተሻለ ቀላል ተፎካካሪ እንደሆኑ ቢናገሩም ሳምንቱን እየተለዋወጡ የመጡት አሀዛዊ መረጃዎች ካማላ ሃሪስ ከባይደን የተሻሉ ብርቱ ተፎካካሪ ሊሆኑ እንደሚችሉ አመላካች ናቸው ተብሏል፡፡