በኢትዮጵያ 42 በመቶ የኤችአይቪ ኤድስ ቫይረስ ተጠቂዎች ራሳቸውን በራሳቸው ማግለላቸው ተገለጸ
በኢትዮጵያ የኤችአይቪ ኤድስ ቫይረስ ስርጭት በመቀነስ ላይ እንደሆነ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል
ቫይረሱ ያለባቸው ህጻናት እና ታዳጊዎች በመገለል ምክንያት መድሃኒት እያወሰዱ አይደለም ተብሏል
በኢትዮጵያ ከኤችአይቪ ኤድስ ቫይረስ ጋር ከሚኖሩ ዜጎች ውስጥ 42 ከመቶዎች እንደሚገሉ ጥናት አመላከተ፡፡
ከ41 ዓመት በገዳይነቱ እና በቫይረስ እንደሚተላለፍ የተለየው የኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ ዘንድሮም ፈዋሽ መድሃኒት ሳይገኝለት ሰዎችን በማጥቃት እና በመግደል ላይ ይገኛል፡፡
ቫይረሱ በኢትዮጵያም በርካቶችን የገደለ ሲሆን ከ618 ሺህ በላይ ዜጎችን ደግሞ ከዚሁ ቫይረስ ጋር እንደሚኖሩ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ ያስረዳል፡፡
የኢትዮጵያ ኤችአይቪ ኤድስ ቫይረስ ያለባቸው ዜጎች ማህበር ከአሜሪካው ጆን ሆፕኪንስ ዩንቨርሲቲ እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሌሎች ተቋማት ጋር ያስጠናውን ጥናት ይፋ አድርጓል፡፡
ይህ ጥናት በመላው ሀገሪቱ የጠደረገ ሲሆን ከ2ሺህ 300 በላይ ሰዎች በጥናቱ ላይ እንደተሳተፉ የማህበሩ ዳይሬክተር ዳይሬክተር አቶ ባይሳ ጫላ ለአልዓይን ተናግረዋል፡፡
እሳቸው እንዳሉት በዚህ ጥናት መሰረት 24 በመቶ የሚሆኑት ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው ወገኖች ዜጎች የቅርብ ዘመዶቻቸውን ጨምሮ በአካባቢያቸው መገለል እንደሚደርስባቸው ተናግረዋል፡፡
42 ከመቶ የሚሆኑት ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ዜጎች ደግሞ ለህክምና ወደ ጤና ተቋማት ሲመጡ ከአገልግሎት ሰጪ አካላት መገለል እንደሚደርስባቸው በጥናቱ ተረጋግጧል ተብሏል፡፡
በተለይም ቫይረሱ ያለባቸው ህጻናት እና ታዳጊዎች በሚደርስባቸው መገለል ምክንያት የጸረ ኤችአይቪ ኤድስ መድሃኒትን ከመውሰድ እያቋረጡ መሆኑ ሁኔታውን የባሰ አሳሳቢ እንደሚያደርገውም ገልጸዋል፡፡
እነዚህ ዜጎች ከአገልግሎት ሰጪዎች፣ ከቅርብ ዘመዶቻቸው እና ከማህበራዊ መስተጋብሮች በሚደርስባቸው መገለል ምክንያት በራሳቸው ራሳቸውን እያገለሉ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጥናቱን በዋቢነት ጠቅሰው ገልጸዋል፡፡
ይህ መሆኑ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በተያዘው ስራ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያደረሰ በመሆኑ ሰዎች ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሰዎችን ከማግለል እንዲቆጠቡም አቶ ባይሳ አሳስበዋል፡፡
በኢትዮጰያ 265 ወረዳዎች ኤችአይቪ ኤድስ ቫይረስ በስፋት ይሰራጭባቸዋል ተብለው የተለዩ ቦታዎች መኖራቸውን እና በነዚህ አካባቢዎች ላይ በልዩ ትኩረት የመከላከል ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ሰምተናል፡፡
አሁን ላይ በኢትዮጵያ የቫይረሱ የስርጭት ምጣኔ 0 ነጥብ 93 የደረሰ ሲሆን ጋምቤላ፣ አዲስ አበባ፣ ሀረሪ እና ድሬዳዋ ደግሞ ከፍተኛ የኤችአይቪ ኤድስ ስርጭት ምጣኔ ያለባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭት እና ጦርነት መኖሩ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ዜጎች መድሃኒታቸውን እንዲያቋርጡ እና ተጨማሪ የቫይረሱ ተጠቂዎች እንዲኖሩ ማድረጉ የቫይረሱን ስርጭት የመከላከል ስራን እንዳከበደም ተገልጿል
የጤና ጥበቃ ሚንስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ከሰሞኑ በሰጡት መግለጫ በኢትዮጵያ የኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ ስርጭት እየቀነሰ መሆኑን ተናግረዋል።
ይሁንና በዓመት በቫይረሱ የሚያዘው ሰው ቁጥር ግን ቀላል ግምት የሚሰጠው እንዳልሆነ የተናገሩት ሚንስትሯ የቫይረሱን መከላከል ስራዎች ተጨማሪ ጥረቶች እንደሚፈልግም ጠቁመዋል።