በኢትዮጵያ “በቀን በአማካኝ 30 ሰዎች በኤድስ ህይወታቸው ያጣሉ” ተባለ
በዓመት ከ11 ሺ 700 በላይ አዳዲስ ሰዎች በቫይረሱ እንደሚያዙም ነው የተገለጸው
ኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታ ነው ተብሎ ከታወቀ 40ኛ ዓመቱን አስቆጥሯል
ኤች.አይ.ቪ/ ኤድስ በዓለማችን ወረርሽኝ በሽታ ነው ተብሎ ከታወቀ በዛሬው ዕለት 40ኛ ዓመቱ ማስቆጠሩን የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 1981 ተከስቶ እስካሁን በርካታ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነ ልቦናዊ ቀውስ ማስከተሉንም እንዲሁ፡፡
ይሁን እንጂ የኤች አይ ቪ ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ የተከሰተውን ቀውስ ለመግታት በርካታ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ መቆየታቸውን ነው የፌደራል ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠርያ ፅ/ቤት የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል በትረ የሚገልጹት፡፡
እስከ በፈረንጆቹ ከ1990 በነበረው የመጀመርያው ዘመን በሽታው እጅግ የተስፋፋበት፣ ትኩረት ያልተሰጠበት፣ በርካቶች ሰለባ የሆኑበት የከፋ ዘመን እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ለአል-ዐይን አማርኛ እንደገለፁት “እ.ኤ.አ በ1994 በሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የሚመራ ም/ቤት ተቋቁሞ ኤች. አይ.ቪን ለመግታት በተሰራ ስራ በሽታው የሚድያ ትኩረት እያገኘ መጥቷል እንዲሁም ከ1995 እስከ 2000 ባሉ ጊዜያት አንፃራዊ ለውጦች ታይተዋል” ብለዋል፡፡
የበሽታው ስርጭት እንዲሁም ኤች. አይ. ቪ በደማቸው በሚገኝ ሰዎች ላይ ይደርስ የነበረውን መገለልና መድልኦ እንደቀነሰም ጭምር በማከል፡፡
ሆኖም ለውጦች ቢኖሩም አሁንም ግን ከ622 ሺ በላይ ዜጎች በደማቸው ውስጥ ቫይረስ እንደሚገኝና የስርጭት ምጣኔው 0.93 በመቶ እንደሆነ ነው አቶ ዳንኤል የሚናገሩት፡፡
በዓለም ጤና ድርጅት መስፈርት መሰረትና ከ0.93 በመቶ የስርጭት ምጣኔው አንፃር በኢትዮጵያ ያለው ወረርሽኙ ስርጭት የከፋ ነው ባይቻልም፤ ከፍተኛ የሆነ ቸልተኝነትና መዘናጋት እየታየ መሆኑ ግን አቶ ዳንኤል አልሸሸጉም፡፡
ስርጭቱ ከክልል ወደ ክልል እንዲሁም ከከተማ ወደ ከተማ ይለያያል የሚሉት አቶ ዳንኤል አሁን ላይ በከተሞች ያለው የስርጭት ምጣኔ ከ3 በመቶ በላይ እንዲሁም በገጠር 0.4 በመቶ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
አቶ ዳንኤል “በቫይረሱ ከተያዙት ከ622 ሺ በላይ ዜጎች መካከል 61 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው”ሲሉ ያስቀምጣሉ ይህ ሴቶች የበለጠ የቫይረሱ ተጋላጭነት ምጣኔ እንዳላቸው የሚያሳይ መሆኑን በመጠቆም፡፡
“ከ100 ሴተኛ አዳሪዎች መካከል 18ቱ ወይም 19ኙ ቫይረሱ ያለባቸው ናቸው” ሲሉም ነው ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ያስቀመጡት፡፡
ከሴቶች በተጨማሪ የረዥም ርቀት አሽከርካሪዎች እና ተንቀሳቃሽ የግንባታ፣ የማዕድን እና አበባ ምርት ሰራተኞች ለበሽታው ተጋላጭ ከሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ስለመሆናቸውም ገልጸዋል፡፡
በዓመት 11 ሺ ወይም በቀን 30 አዳዲስ ሰዎች (67 በመቶ የሚሆኑት ከ15 እስከ 24 የዕድሜ ክልል የሚገኙ) በቫይረሱ እንደሚያዙ፤ በየዓመቱ 12ሺ ወይም በየቀኑ 30 ሰዎች እንደሚሞቱም አስታውቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ የቫይረሱ የስርጭት ታሪክ 1996 ዓ/ም ከፍተኛ የሟቾች ቁጥር የተመዘገበበት ዓመት ነው፡፡ 90 ሺ ያህል ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸውን ማጣታቸውም ይነገራል፡፡
ተቋማቸው የማስተባበር ኃላፊነቱን ለመወጣት እየሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ ዳንኤል በሽታው ሁሉን አቀፍ ጥረት የሚፈልግ በመሆኑ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ኃላፊነታቸው እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡