የምናስነጥሰው ለምንድን ነው? ንጥሻን ለማስቆም መሞከርስ ምን ጉዳት አለው?
በስኮትላንድ አፍና አፍንጫውን በማፈን ላለማስነጠስ የሞከረው ግለሰብ ከባድ ጉዳት ደርሶበታል

የህክምና ባለሙያዎች ንጥሻን መከላከል በጆሮ ታምቡርና በጉሮሮ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል አሳስበዋል
ንጥሻ ወደ መተንፈሻ አካላት የሚገባ ጎጂ ነገርን ለመከላከል ሰውነታችን በተፈጥሮው የሚሰጠው ምላሽ ነው።
ስናስነጥስ አፍና አፍንጫችን በክርናችን ወይም በእጃችን መሸፈንና እጃችን መታጠብም የተላላፊ ቫይረሶችን ስርጭት ለመቀነስ እንደሚያግዝ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ይህን ተፈጥሯዊ ሂደት ማስቆምም ከባድ የጤና ችግር እንደሚያስከትል ይገልጻሉ።
በስኮትላንድ ዱንዴ በተባለ አካባቢ ንጥሻን ለማስቆም የሞከረ ግለሰብ ራሱን ስቶ ሆስፒታል መግባቱም የጉዳዩን አሳሳቢነት አሳይቷል።
ስሙ ያልተጠቀሰውና በ30ዎቹ የእድሜ ክልል የሚገኘው ግለሰብ አፉንና አፍንቻውን ዘግቶ ንጥሻውን ለማስቆም በመሞከሩ ነው በጉሮሮው ላይ ጉዳት የደረሰበት።
በከተማዋ የኒንዌልስ ሆስፒታል የህክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት፥ ንጥሻን ለማስቆም አፍና አፍንጫን በተመሳሳይ ማፈን በላይኛው የመተንፈሻ አካል ላይ የሚፈጠር ግፊትን በ20 እጥፍ ይጨምራል።
ይህም በጆሮ ታምቡር፣ በጉሮሮ እና ከበድ ሲልም በአይንና በጆሮ የደም ቱቦዎች ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ ነው የተናገሩት።
መኪና እያሽከረከረ እያለ ንጥሻን ለማቆም የሞከረው ወጣት ምርመራ ሲደረግለት በጉሮሮው ላይ 2 ሚሊሜትር የሚረዝም ክፍተት መገኘቱ ተገልጿል።
ግለሰቡ ቀዶ ህክምና ባያስፈልገውም ለቀናት ህክምናውን ተከታትሎ ከሆስፒታል ወጥቷል፤ ለሁለት ሳምንትም ከባድ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ እንዳያደርግ ታዟል።
እምብዛም የማይከሰተው አደጋ በስኮትላንዳዊው ወጣት ታይቷል የሚሉት ዶክተር ራሳድ ሚሲሮቭስ፥ ከግለሰቡ ድርጊት መማር እንደሚገባ ያሳስባሉ።
“እንደ ሳይነስ እና አለርጂ ያሉ ችግሮች ንጥሻን ቢያበዙና ሰዎችን ቢያማርሩም ንጥሻን ለማስቆም መሞከር ግን አደገኛ ነው” የሚሉት ዶክተር ሚሲሮቭስ፥ ንጥሻን ማስቆም ሳይሆን በዚሁ ጊዜ የሚወጣን ቫይረስ ወደሌሎች እንዳይሰራጭ በእጅና ክርን መሸፈኑ ሁሌም ሊዘነጋ አይገባም ብለዋል።
በ2018 በሌስተር መሰል ሙከራ ያደረገ ግለሰብ ጉሮሮው ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል።