በኢትዮጵያ ውዱ ህክምና ምን ይመስልዎታል?
በኢትዮጵያ የአዕምሮ ህመም እየተስፋፋና በዛው ልክ ትኩረት ያልተሰጠው የማህበረሰብ ጤና እክል ሆኗል- ባለሙያ
የባለሙያዎች እጥረት፣ የማገገሚያ ማዕከላት፣ የህክምና መስጫ ሆስፒታሎችና መድሃኒት እጥረት ለዋጋው መወደድ ምክንያት ነው
በኢትዮጵያ የአዕምሮ ህመም እየተስፋፋና በዛው ልክ ትኩረት ያልተሰጠው የማህበረሰብ ጤና እክል እየሆነ መምጣን የዠርፉ ባለሙያ ይናገራሉ።
ታሪኳን ለአል ዐይን አማርኛ ያጋራች ስሟ እንዳይጠቀስ የፈለገች የአዕምሮ ህመምተኛ “የአዕምሮ ህመምተኛ እንደሆንኩ አላውቅም ነበር፤ለምን ይህ አልሆነም እያልኩ አለቅስ ነበር፣ ቤተሰቦቼ አይወዱኝም ብዬም አስባለሁ፣ ለሁሉም ጥፋቴ በዙሪያዬ ባሉ ሰዎች ላይ አመካኝ ነበር” ትላለች።
“ባንድ ጓደኛዬ እርዳታ ከአንድ የአዕምሮ ሀኪም ጋር ተገናኝቼ ህክምናውን አገኘሁ” የምትለው ይህች ባለታሪክ” ህክምናውን ካገኘችጊዜ ጀምሮ ደስተኛ እና አመስጋኝ መሆኗን ነግራናለች።
“ህክምናውን ባለመረዳቴ አልያም ቤተሰቦቼን ጨምሮ ብዙዎች ወደ አዕምሮ ህክምና እንድሄድ ባለማድረጋቸው ለብዙ ዓመታት ህይወቴ በስቃይ የተሞላ እንዲሆን አድርጎት ነበር፣ባንድ ወቅት ራሴን ላጠፋ ጫፍ ላይ ደርሼ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ወደ ጤናዬ ተመልሼ ስራዬን እና ህይወቴን በሚገባ እየመራሁ ነው” ብላለች።
“ይሁንና ህክምናው ውድ እና ቀጣይነት ያለው በመሆኑ ለማማከር እና መድሃኒት ዋጋ በሳምንት ከ800 ብር እስከ 2ሺህ ብር እያወጣሁ ነው ይህ እጅግ እየፈተነኝ ነው” ብላናለች።
አንድ ዜጋ ማንኛውንም አይነት ህመም ተሰምቶት በቀላሉ ባቅራቢያው ወዳለ የህክምና ተቋም ሄዶ እንደሚታከመው ሁሉ የዓዕምሮ ህመም ህክምናም ሊቀል ይገባል፣ ለዚህ ደግሞ መንግስት ለሌሎች ህመሞች ትኩረት በሰጠው ልክ ለአዕምሮ ህመም ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቃለች።
ወላጆች እና ማህበረሰቡ ጋር ስለ አዕምሮ ህመም ያለው አስተሳሰብ ትክክል አለመሆኑን የምትናገረው ይህች ባለታሪክ ሰዎች የአዕምሮ ህመም ሲያጋጥማቸው ታክመው መዳን እንደሚችሉ ማመን አለባቸውም ብላለች።
ብዙዎች ሰዎች በአመለካከት እና ተስፋ በመቁረጣቸው ምክንያት ራሳቸውን የሚያጠፉ፣ ቤት ተዘግቶባቸው በጨለማ የሚኖሩ እና በየቤተ እምነቶች ከነ ስቃያቸው የሚኖሩ እንዳሉም ነግራናለች።
ቤተሰቦቼ የተማሩ የሚባሉ ቢሆንም የአዕምሮዬ ጤና ሲታወክ ሰይጣን ይዟት ነው፣ ጸባያዋ ተበላሸ እና ትታሰር ይሉ ነበር የምትለው ይህች ባለታሪክ ስለ ህመሙ ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ በሰፊው ማስተማር እንደሚያስፈልግም ጠቁማለች።
በአዲስ አበባ የአዕምሮ ህክመና እና ማማከር አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት የስነ ልቦና እና የማህበረሰብ ጤና አማካሪ ሙሉ መኮንን፤ የአዕምሮ ህመም እየተስፋፋ እና በዛው ልክ ትኩረት ያልተሰጠው የማህበረሰብ ጤና እክል መሆኑን ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
አንድ ሰው የዕለት ተዕለት ጉዳዩን መፈጸም ሳይችል ሲቀር የአዕምሮ ህመም አጋጥሞታል ይባላል የሚሉት አማካሪዋ ሰዎች እንዲህ አይነት ነገር ሲገጥማቸው ሳይብስ ወደ አዕምሮ ሀኪም ጋር እንዲሄዱ አሳስበዋል።
እንደ አማካሪዋ ገለጻ በኢትዮጵያ የአዕምሮ ህመምተኞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ብዙ አስረጂ ማስረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን ጭንቀት፣ ድብርት፣ ተስፋ መቁረጥ እየተሰማቸው የሚመጡ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ጠቁመዋል።
ይሁንና የአዕምሮ ህመም የሚፈልገው ዜጋ ቁጥር እየጨመረ የመምጣቱን ያህል በመንግስት የተሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መሆኑንም አማካሪዋ ጠቁመዋል።
የባለሙያዎች እጥረት፣ የማገገሚያ ማዕከላት፣ የተኝቶ ህክምና መስጫ ሆስፒታሎች እና መድሃኒት አስመጪዎች ጥቂት ናቸው የሚሉት ሙሉ መኮንን ከምንም በላይ ግን ህብረተሰቡ ስለ አዕምሮ ህመም ያለውን ግንዛቤ ማስተካከል የሚያስችል ትምህርት መሰጠት አለበትም ብለዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በጉዳዩ ዙሪያ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በነበራው ቆይታ፤ በኢትዮጵያ በጦርነቱ እና በሌሎች የማህበራዊ ቀውሶች ምክንያት የስነ ልቦና ድጋፍ የሚፈልጉ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ከአዕምሮ ህመም ጋር ተያይዞ ህክምናውን ለሚፈልጉ ዜጎች የሚውሉ መድሃኒት እጥረቶች ነበሩ የሚሉት ሚኒስትሯ አሁን ላይ ከአቅራቢዎች ጋር በተሰራው ስራ ችግሩ በመቃለል ላይ መሆኑንም አክለዋል።
የአዕምሮ ህመም በቀላሉ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ በሁሉም ሆስፒታሎች የስነ ልቦና ባለሙያ ለማሟላት እየተሞከረ መሆኑን አክለዋል።
በአጠቃላይ ግን በሚሹ የጦርነት እና ግጭት አካባቢዎች በልዩ መልኩ ባለሙያ እየተደራጀ ነው የተባለ ሲሆን በሌሎች መደበኛ እንቅስቃሴዎች ባሉባቸው አካባቢዎች ደግሞ ስለ አዕምሮ ህመም ምንነት፣ ህክምናው እና ሌሎች ተያያዥ አገልግሎቶች ቀስ በቀስ እንዲሟሉ ይደረጋሉም ተብሏል።
በዓለማችን ከአጠቃላይ ህዝብ ቁጥር ውስጥ 970 ሚሊዮን ያህሉ የአዕምሮ ህመምተኞች ሲሆን በየዓመቱም ስምንት ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ በዚሁ ህመም ምክንያት ህይወታቸውን ያጣሉ።
በየዓመቱ ህይወታቸው ከሚያልፉ አጠቃላይ ዜጎች ውስጥም 14 በመቶ ያህሉ የአዕምሮ ህመምተኞች እንደሆኑ የዓለም ጤና ድርጅት ከአምስት ወራት በፊት ያወጣው ሪፖርት ያስረዳል።