በርዕደ መሬቱ የተጎዱ ዜጎችን ህይወት የማትረፉ ተግባር አድካሚ እየሆነ መምጣቱን የነፍስ አድን ሰራተኞች ገለጹ
በአማጺያን ስር ወደ ሚገኘው ሰሜን ምእራብ ሶሪያ የሚላከው ርዳታ በቂ አይደለም ተብሏል
ቱርክ እና ሶሪያን በመታው ርዕደ መሬት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ33 ሺህ በላይ ደርሷል
በቱርክ የሚገኙ የነፍስ አደን ሰራተኞች ብዙ ሰዎችን ከፍርስራሽ ህንጻዋች እያወጡ ቢሆንም ፤ የደረሰው አደጋ መጠነ ሰፊ በመሆኑ በርዕደ መሬቱ የተጎዱ ዜጎችን ህይወት የማትረፉ ተግባር አድካሚ እየሆነ መምጣቱ ገልጸዋል፡፡
በተለይም ርዕደ መሬት በመታቸው አከባቢዎች ያለው ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ የተጎዱ ዜጎችን ህይወት ለማትረፍ የሚደረገውን ጥረት እያስተጓጎለ ነው ብለዋል፡፡
በሬክተር ስኬል 7.8 ሆነ የተመዘገበውን ርዕደ መሬት ተከትሎ ህወታቸው ካለፈው በአስር ሺዎች ከሚቆጠሩ ሰዎች ባሻገር፤ በርካታ ሰዎች በፍርስራሾች ውስጥ እንደሚገኙም ነው የገለጹት ሰራተኞቹ፡፡
ሮይተርስ አንድ የነፍስ አድን ሰራተኛን ጠቅሶ እንደዘገበው በአንታክያ በርካታ በከረጢት የታሸጉ አስክሬኖች በከተማው ጎዳናዎች ላይ ተዘርግተው ቢታዩም አሁንም ብዙዎች በፍርስራሽ ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ስለ ጉዳዩ ቀጣይ አቅድ የተጠየቁት የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ባለስልጣናት ፈጣን ምላሽ መስጠት ነበረባቸው ብለዋል።
“በሳምንታት ውስጥ” ከተሞችን መልሶ የመገንባት ስራ እንደሚጀምርም ቃል ገብተዋል ፕሬዝዳንቱ።
በተጨማሪም አደጋው በደረሰባቸው ከተሞች አካባቢ የሚስተዋለው ዝርፊያ የኮነኑት ፕሬዝዳንቱ፤ በዘረፋ ላይ እየተሳተፉ ያሉትን ሰዎች አስጠንቅቀዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በርዕደ መሬቱ በተመታውና በአማጺያን ቁጥጥር ስር በሚገኘው ሰሜን ምእራብ ሶሪያ ያለው ሁኔታ እጅግ ከባድ መሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡
ለአመታት በዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት ሲፈናቀሉ የቆዩት ሶሪያውያን አሁንም ቤት አልባ ሆነዋል፡፡
ከሰኞ ጀምሮ በደርዘን የሚቆጠሩ የእርዳታ አውሮፕላኖች በሶሪያ መንግስት በተያዙ አካባቢዎች መድረስ ቢችሉም፤ በአማጺያኑ ስር ወደ ሚገኘው ሰሜን ምዕራብ አከባቢ ማድረስ አለመቻሉ ተገልጿል፡፡
በሬክተር ስኬል 7.8 በተመዘገበው የርዕደ መሬት አደጋ ኩፉኛ ወደ ተጎዳችው ሶሪያ አሌፖ ከተማ ያቀኑት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ያለው ሁኔታ በጣም ከባድ መሆኑ ተናግረዋል፡፡
“ከርዕደ መሬት አደጋው የተረፉ ሰዎች ያሉበት ሁኔታ ሳይ በጣም አዝኛለሁ”ም ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ፡፡
ከአደጋው የተረፉት ሰዎች “በቂ የመጠለያ፣ የምግብ፣ የውሃ፣ ኤሌክትሪክ እና የህክምና አገልግሎት አለማግኘታቸው የሚያሳዝን ነውም ነው”ም ብለዋል፡፡
በአደጋው ወላጆቻቸውን ያጡ ኑርን እና ዑመር የተባሉ ሶሪያውያን ማናገራቸውን የገለጹት ዶ/ር ቴድሮስ፤ “የሚደርስባቸውን ስቃይ የሚገልጹ ቃላት የሉም” በማለትም ያለውን ችግር አስከፊነት ገልጸውታል፡፡
ቱርክ እና ሶሪያን በመታው ርዕደ መሬት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ33 ሺህ በላይ መድረሱ እየተገለጸ ነው፡፡
በተጨማሪም ከ23 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በአደጋው ምክንያት ለተለያዩ ችግሮች ተዳርገው እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአደጋው መጠንና ያስከተለው ጉዳት በግልጽ ለማወቅ አለመቻሉ የገለጸው ከቀናት በፊት ነበር፡፡
በተለይም በጦርነት ቀውስ ውስጥ ተዘፍቃ በቆየችው ሶሪያ ላይ ያለው የአደጋ መጠን ለማወቅ መቸገሩ ተመድ ገልጿል፡፡
የድርጀቱ ዋና ጸሃፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የአደጋው መጠን እጅግ ከባድ መሆኑ "አሁን እየተገለጠልን ነው" ሲሉ ማስጠንቀቃቸው አይዘነጋም፡፡
የጸጥታው ምክር ቤት በተለያዩ መስመሮች እርዳታ ወደ ሶሪያ የሚገባበት አማራጭ እንዲፈልግም ጥሪ አቅርበዋል ዋና ጸሃፊው፤ አሁን ላይ ከቱርክ ወደ ሰሜን ምእራብ ሶሪያ ሰብዓዊ እርዳታ መላክ መጀመሩን እንደ ጥሩ እርምጃ በማንሳት፡፡
"አሁን ፖለቲካ የሚሰራበት ወቅት ሳይሆን አንድነት የሚያስፈልግብት ወቅት ላይ ነው ያለነው” ሲሉም ነው የተናገሩት ዋና ጸሃፊው፡፡