ሊዮነል ሜሴ በፓሪስ ኦሎምፒክ ለሀገሩ እንዲጫወት በሩ ክፍት መሆኑን የአርጀንቲናው ከ23 አመት በታች ቡድን አሰልጣኝ ጃቪየር ማሸራኖ ተናግሯል
ሜሲ በፓሪስ ኦሎምፒክ እንዲጫወት ግብዣ እንደሚቀርብለት ማሸራኖ ተናግሯል።
ሊዮነል ሜሴ በፓሪስ ኦሎምፒክ ለሀገሩ እንዲጫወት በሩ ክፍት መሆኑን የአርጀንቲናው ከ23 አመት በታች ቡድን አሰልጣኝ ጃቪየር ማሸራኖ ተናግሯል።
በደቡብ አሜሪካው የኦሎምፒክ ማጣሪያ ጨዋታ ብራዚልን 1-0 በማሸነፍ የመጨረሻ አራቱ ቡድን ውስጥ መካተት ችላለች።
ይህን ተከተሎ ብራዚል ከፈረንጆቹ 2004 ወዲህ ለኦሎሞፒክ ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ ማለፍ ሳትችል ቀርታለች።
የ36 አመቱ ሜሲ በፓሪስ ኦሎምፒክ ጨዋታ ይሳተፍ እንደሆነ የተጠየቀው የቀድሞው የሜሲ የአርጀንቲና እና የባርሴሎና ጓደኛው ማሸራኖ "ከሊዮ ጋር ያለኝን ግንኙነት ሁሉም ያውቃል"ብሏል።
"እንደ ሌዮ ላሉ ተጨዋቾች በሩ ክፍት ነው። ከቡድናችን ጋር ሆኖ እንዲሄድ እንፈልጋለን። ነገርግን እሱ ጊዜ ካለው እና ማመቻቸት ከቻለ የሚሆን ነው፣ ግብዣ ግን ይደረግለታል።"
አርጀንቲና በ2022 በኳታር የተካሄደውን የአለም ዋንጫ እንድታነሳ ያደረገው የሚያሚው አጥቂ ሜሲ፣ በቤጂንግ በተካሄደው ኦሎምፒክ ጨዋታ ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር በመሆን ዋንጫ አንስቷል።
ዋና ዋናዎቹ የኦሎምፒክ እግርኳስ ጨዋታዎች በሐምሌ እና በነሐሴ የሚካሄዱ ናቸው።
ተሳታፊ ቡድኖች ሶስት በእድሜ የገፉ ተጨዋቾችን ማሳተፍ ይችላሉ።
በፓሪስ የሚካሄደው የኦሎምፒክ ጨዋታ ከፈረንጆቹ ሐምሌ 26 እስከ ነሐሴ 11፣ 2024 ድረስ እንደሚካሄድ የወጣው መርሀግብር ያሳያል።