የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በንጽሃን ሰዎች ላይ የደረሰውን “ጭፍጨፋ”ማውገዙን ገለጸ
የምክርቤቱ አባላት ያደረጉት ስብሰባ ለሚዲያ ዝግ ነበር
የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በምእራብ ወለጋ እና በሌሎች አካባዎች በንጹሃን ላይ የደረሰውን ጭፍጨፋ አውግዟል
የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት፤ የም/ቤቱ አባላት ሰሞኑን በምዕራብ ወለጋ እና በሌሎች አካባቢዎችም “በአሸባሪው ሸኔ እና ሌሎች መሰል ተላላኪ ጽንፈኛ ኃይሎች አማካኝነት” በንጹሐን ዜጐች ላይ የደረሰውን ጭፍጨፋ “በጽኑ እናወግዛለን” ማለታቸውን ገልጿል፡፡
ረቡዕ ዕለት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተር እና የፌደራል ፓሊስ ኮሚሽር ጀነራል፤ በምዕራብ ወለጋው የዜጎች ጭፍጨፋ ዙሪያ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር ተነጋግረዋል፡፡
የምክርቤቱ አባላት ከመንግስት ኃላፊዎች ጋር ያደረጉት ስብሰባ ለሚዲያ ዝግ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
የምክር ቤት አባላቱ ውይይት ያደረጉት ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተር እንደሻው ጣሰው እና ከፌደራል ፓሊስ ኮሚሽር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ጋር መሆኑንም ምክር ቤቱ በይፋዊ የማህበራዊ መገናኛ ገጹ አስታውቋል፡፡
ምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ በሚያደርግበት ዕሙስ እለት ደግሞ የመንግስት ተጠሪው ተስፋዬ በልጅጌ በምዕራብ ወለጋው የዜጎች ጭፍጨፋ፤ ብልጽግናን ወክለው ፓርላማ ከገቡ አባላት ጋር መነጋገራቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ዜጎች በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ መገደላቸው ከተገለጸ ወዲህ ም/ቤቱ አንድ መደበኛ ስብሰባ ቢያደርግም ከዛ በኋላ ማክሰኞና ሃሙስ የሚደረጉ የም/ቤት መደበኛ ስብሰባዎች አልተካሄዱም፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ ወለጋ ላይ የተገደሉ ዜጎችን ጉዳይ በአጀንዳነት እንዲይዝ ም/ቤት ባሉ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አባላት ቢጠየቅም ይህንን ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ አባላቱ ማክሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2014 ዓ/ም ምክር ቤቱ ወለጋ ላይ የተገደሉ ዜጎችን ጉዳይ በአጀንዳነት እንዲይዝ ቢጠይቁም አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ግን ጥያቄውን ሳይቀበሉ በመቅረታቸው ስብሰባውን ረግጠው መውጣታቸው ይታወሳል፡፡