የአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት ለሁለተኛ ጊዜ በትራምፕ ላይ ኢምፒችመንት ለማካሔድ ሩጫ ላይ ነው
የትራምፕ ደጋፊዎች ከፈጸሙት የአመጽ ድረጊት ጋር በተያያዘ ፣ የአሜሪካ ምክር ቤት ፕሬዝዳንቱ በ25ኛው የአሜሪካ ሕገ መንግሥት ማሻሻያ መሰረት ከስልጣን እንዲወርዱ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ይሁንና ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ ፣ ሀገሪቱን በአግባቡ መምራት ያልቻለ ፕሬዝዳንንት ከስልጣኑ ተነስቶ ምክትሉ መሪነቱን እንዲረከብ የሚደነግገውን 25ኛውን ማሻሻያ እንደማይተገብሩት ገልጸዋል፡፡
ይህን ተከትሎ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንቱን በኢምፒችመንት ከስልጣን ለማውረድ ሽር ጉዱን ጀምሯል፡፡ ምክር ቤቱ አመጽ በመቀስቀስ ወንጀል ፕሬዝዳንቱን ለመክሰስ ዛሬ ድምጽ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህም ፕሬዝዳንት ትራምፕን በአሜሪካ ታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ ኢምፒችመንት የሚካሄድባቸው የመጀመሪያው መሪ ያደርጋቸዋል፡፡
ምንም እንኳን ትራምፕ ከኋይት ሀውስ ለመውጣት የቀራቸው የአንድ ሳምንት እድሜ ብቻ ቢሆንም ፣ ፕሬዝዳንቱ በኢምፒችመንት እንዲነሱ ባለቀ ሰዓት ሩጫ መጀመሩ ፣ በዋነኛነት ከዚህ በኋላ ለፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዳይቀርቡ ለማድረግ በማሰብ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም የፕሬዝዳንቱ ቁልፍ ደጋፊ የሆኑ ሪፓብሊካን የምክር ቤት አባላት ፣ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢምፒችመንት ከስልጣን እንዲነሱ ድምጻቸውን እንደሚሰጡ በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡ በተለይ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ደጋፊዎቻቸው የፈጸሙትን የአመጽ ድርግት አለማውገዛቸው እና ከዚሁ ጋር በተያያዘ ያደረጉት እና የተናገሩት ሁሉ ትክክል መሆኑን መግለጻቸው የራሳቸውን ሰዎችም ጭምር ያስቆጣ ተግባር ሆኗል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፣ ዩቲዩብ የተሰናባቹ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቻናል ለሰባት ቀናት አዲስ ተንቀሳቃሽ ምስል እንዳይጫንበት ማገዱን አስታወቀ፡፡ ኩባንያው እርምጃውን የወሰደው የእርሳቸው ቻናል ለሌላ አመጽ እንዳያነሳሳ በመስጋት መሆኑን ዩፒአይ ዘግቧል፡፡ የትራምፕ ደጋፊዎች ያደረጉት ኃይል የተቀላቀለበት አመጽ በድጋሚ ሊኖር ይችላል የሚል ስጋት እንዳለውም ነው ኩባንያው የገለጸው፡፡
ከዚህ ቀደም ፌስቡክ ፣ ኢንስታግራምና ትዊተር የትራምፕን ገጾች ማገዳቸው የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ ዩቲዩብ በተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ቻናል ላይ የመጀመሪያ እርምጃ ወስዷል፡፡
ዩቲዩብ በትዊተር ገጹ ላይ እንዳለው በዶናልድ ትራምፕ ቻናል ላይ ለሚቀጥሉት ሰባት ቀናት አዲስ ተንቀሳቃሽ ምስል አይጫንም፡፡
የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች በአሜሪካ የሕግ መወሰኛና የሕግ መምሪያን ጨምሮ ብዙ ተቋማት ወደሚገኙበት ካፒቶል ሂል በማምራት የጉልበት አመጽ ማድረጋቸውን ተከትሎ የአሜሪካ የቴክኖሎጅ ኩባንያዎች የዶናልድ ትራምፕን ገጾች በቋሚነትና በጊዜያዊነት እያገዱ ነው፡፡ ከቀናት በፊት ትዊተር የፕሬዝዳንቱን ገጽ በቋሚነት መዝጋቱ ይታወሳል፡፡