የተወካዮች ምክርቤት በዛሬው እለት ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ የሚኒስትሮች ምክርቤት የውሳኔ ሀሳብን በአብላጫ ድምጽ በ16 ተቃውሞ እና በ12 ድምጽ ተአቅቦ ማጽደቁን ምክርቤቱ ገልጿል
የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት በአማራ ክልል እና እንደአስፈላጊቱ በሌሎችም ቦታዎች ተግባራዊ ይሆናል የተባለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማጽደቁን ምክርቤቱ በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል።
የሚንስትሮች ምክርቤት በአማራ ክልል በትጥቅ የተደገፈ እንቅስቃሴ መኖሩን እና ይህንንም በመደበኛው የህግ ስርአት መቆጣጠር የማይቻልበት ሁኔታ መፈጠሩን በመግለጽ ነበር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ የወሰነው።
የተወካዮች ምክርቤት በዛሬው እለት ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ የሚኒስትሮች ምክርቤት የውሳኔ ሀሳብን በአብላጫ ድምጽ በ16 ተቃውሞ እና በ12 ድምጽ ተአቅቦ ማጽደቁን ምክርቤቱ ገልጿል።
ምክርቤቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቦርድ አባላትን እና ሰብሳቢዎችንም መርጧል።
በአማራ ክልል፣ በፌደራል መንግስት የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተፈጠው ግጭት ንጹሃን ሰዎች እንዲገደሉ ምክንያት መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ) ዛሬ ባወጣው ሪፖርት ገልጿል።
በክልሉ ባሉ በርካታ ከተሞች ንጹሃን ሰዎች ከቤታቸው ውጭ ወይም መንገድ ላይ ተገድለዋል ብሏል ኢሰመኮ።
ኢሰመኮ ተፋላሚ ሀይሎች ያለምንም ቅደመ ሁኔታ ግጭቶችን እንዲያቆሙ፣ ለሰላማዊ ንግግር ቦታ እንዲያመቻቹና ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ አሳስቧል።
የፌደራል መንግስት በክልሉ "የህግ ማስከበር" ስራ እየሰራ መሆኑን እና የተወሰኑ የክልሉ ከተሞች ወደቀደመ ሰላማቸው መመለሳቸውን መግለጹ ይታወሳል።