ምክርቤቱ መንግስት በትግራይ ክልል “ጊዜያዊ አስተዳደር” እንዲመሰርት ወሰነ
ኢሰመኮ የጸጥታ ሃይሎች የሰላማዊ ሰዎችን ደህንነት እንዲያከብሩ መጠየቁ ይታወሳል
ምክርቤቱ የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል ጣልቃ እንዲገባና ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲመሰርት ወሰኔ አሳለፈ
ምክርቤቱ የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል ጣልቃ እንዲገባና ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲመሰርት ወሰኔ አሳለፈ
የፌደሬሽን ምክርቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የፌደራል መንግስት ”በህገወጡ የትግራይ ክልል መንግስት” ጣልቃ እንዲገባና ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲያቋቁም ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ምክርቤቱ “ህገወጡ የትግራይ ክልል መንግስት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ላይ በክልሉ በሚገኘው ጀግናው የአገር መከላከያ ሠራዊት” እና በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች “አስነዋሪ ጥቃት” መፈጸሙን ገልጿል፡፡
ምክርቤቱ “በትጥቅ የተደገፈ የአመጽ እንቅስቃሴ ማድረግ፤ ከሌላ ክልል ወይም ከሌላ ክልል ብሔር፣ ብሄረሰብ ወይም ሕዝብ ጋር የተፈጠሩ ችግሮችን ሰላማዊ ባልሆነ መንገድ መፍታት፤ የፌዴራሉን ሰላምና ጸጥታ ማናጋት…” “ህገወጡ የትግራይ ክልል መንግስት” የፈጸማቸው የህገመንግስት ጥሰቶች ናቸው ብሏል፡፡
“ህገመንግስቱን አደጋ ላይ የጣለውን ድርጊት ለማስቆም፤ ህገውጡን የክልል ምክርቤትና ከፍተኛ ስራ አስፈጻሚ አካል ታግዶ ለፌደራል መንግስት ተጠሪ እንዲሆን ለማድረግ” እንዲቻል የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ መወሰኑን ምክርቤቱ አስታውቋል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ጠቅላይ ሚኒስት ዐቢይ አህመድ ህወሓት በትግራይ ክልል በሚገኘው መከላከያ ላይ ጥቃት ማድረሱን ካስታወቁና እርምጃ እንደሚወስድ ከተናገሩ በኋላ በፌደራልና በትግራይ መካከል ያለው ጦርነት እየተካሄደ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትናንትናው እለት በሰጡት መግለጫ በክልሉ የሚገኙና ህወሃት ሊጠቀምባቸው ይችላል የተባሉት 300 ኪ.ሜ መወንጨፍ የሚችሉትን ሮኬቶችን በአየር ሃይል መውደማቸውን ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡
በፌደራል መንግስትና በትግራይ ክልል ያለው አለመግባባት የጀመረው ኢትዮጵያን ለ27 አመታት ሲመራ የነበረው ኢህአዴግ ከሁለት አመትበፊት ፈርሶ ብልጽግና ፓርቲ ሲመሰረት ፣ ከመስራቾቹ አንዱ የነበረው ህወሓት የውህደቱ አካል አልሆንም ባለበት ወቅት ነበር፡፡
የፌደራል መንግስት በኢትዮጵያ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ምርጫ ለማካሄድ አያስችልም በማለት ምርጫ እንዲራዘም ሲያደርግ፣ ህወሓት በራሱ ክልልዊ ምርጫ አድርጎ ነበር፡፡
ህወሓት የፌደራል መንግስት ምርጫ ማካሄድ ሲገባው ከህገመንግስቱ ውጭ ነው ስልጣን ላይ ያለው ሲል ሲከስ ቆይቷል፡፡ መንግስትን የሚመራው ብልጽግና ፓርቲ በበኩሉ የህወሓት ምርጫ ተቀባይነት እንደሌለው ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
የፌደራል መንግስት ከሳምንታት በፊት ከትግራይ ክልል ጋር ህጋዊ ግንኙነት ማቋረጡን አስታውቆ ነበር፡፡አሁን ላይ በፌደራል መንግስትና በትግራይ ክልል መካከል የነበረው አለመግባባት ሁኔታው ተባብሶ ወደ ግጭት ሊያመራ ችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንና(ኢሰመኮ) አለማአቀፉ ማህበረሰብ የጸጥታ ሃይሎች ሰላማዊ ዜጎች እንዳይጎዱና ግጭቱ እንዲረግብ አሳስበዋል፡፡