የመከላከያ ሰራዊት በመጀመሪያ ዙር እርምጃው ያቀዳቸው ሶስት ዓላማዎች ሙሉ በሙሉ መሳካታቸውን ጠ/ሚ ዐቢይ ገለጹ
የትግራይ ክልል ር/መስተዳድር የክልሉ ኃይል የፌዴራሉን ጦር የመመከት ሙሉ ቁመና ላይ እንደሚገኝም መግለጻቸው ይታወሳል
አየር ኃይል በወሰደው እርምጃ ሮኬቶችን ጨምሮ ሌሎች ከባድ የጦር መሳሪያዎችን መውደማቸውን ጠ/ሚኒስትሩ ተናግረዋል
የመከላከያ ሰራዊት በመጀመሪያ ዙር እርምጃው ያቀዳቸው ሶስት ዓላማዎች ሙሉ በሙሉ መሳካታቸውን ጠ/ሚ ዐቢይ ገለጹ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ምሽት ላይ በሰጡት መግለጫ “ስግብግቡ ጁንታ” ባሉት የሕወሓት ኃይል ላይ የተደረገው የመጀመሪያው ዙር ኦፕሬሽን በስኬት እንደተጠናቀቀ ገልጸዋል፡፡ መከላከያ ሰራዊት በወሰደው የመጀመሪያው ዙር እርምጃ 3 ዓላማዎች እንደነበሩት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከነዚህም የመጀመሪያው “የጠላትን ጥቃት መግታት ነበር” ብለዋል፡፡
“ጠላት” ጥቃት በሚሰነዝርባቸው አካባቢዎች የመከላከያ ሰራዊት በስፋት እንዳልነበረ ጠቅሰው አሁን ላይ ከያለበት ኃይል በማንቀሳቀስ ሙሉ የሎጂስቲክስ እና የኃይል አቅርቦት ስለመጠናቀቁም ነው የተናገሩት፡፡
“የጠላትን ጉዞ ሙሉ በሙሉ መግታት እና ተጨማሪ ጥቃት ማድረስ ወደ ማይችልበት ደረጃ አድርሰነዋል” ሲሉም ነው የገለጹት፡፡
ሁለተኛው ዓላማ ጥቃት የደረሰበትን የመከላከያ እና የፌዴራል ፖሊስ ኃይል እንዲሁም ወሳኝ ሀገራዊ ሀብቶች እና ትጥቆችን መታደግ መሆኑን በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡ ከዚህ አንጻርም “በባድመ ፣ በጾረና ፣ በዛለአንበሳ በዋና ዋና ቦታዎች ላይ ተሰማርተው የነበሩ የሰራዊት አባላት እና ትጥቆቻቸው ሙሉ በሙሉ ከ”ጠላት ፍላጎት ውጭ ሆነዋል” ብለዋል፡፡ መከላከያው አሁን ሙሉ በሙሉ ጥቃት መሰንዘር ወይም መከላከል ወደሚችልበት ቁመና ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡፡
ሶስተኛው ዓላማ የ”ጠላትን ኃይል” የማድረግ አቅም ማዳከም ሲሆን የየኢትዮጵያ አየር ኃይል በወሰደው እርምጃ በተለያዩ ስፍራዎች ላይ የነበሩ ሚሳይሎችን እና ሮኬቶችን ጨምሮ ሌሎች የተለያዩ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ሙሉ በሙሉ ማውደም መቻሉን ገልጸዋል።
እነዚህ ሮኬቶች እስከ 300 ኪሎ ሜትሮች መወንጨፍ የሚችሉ በመሆናቸው እና ሕወሐት ሮኬቶቹን የመጠቀም ፍላጎት ስላለው በመቐለ እና አካባቢዋ በነበረው የከባድ መሳሪያ ማስቀመጫ ላይ የአየር ኃይሉ እርምጃ እንዲወስድ መደረጉ በጠ/ሚኒስትሩ ተገልጿል።
ሶስቱም ዓላማዎች ሙሉ በሙሉ መሳካታቸውንም ነው የተናገሩት፡፡ አንድ አንድ አካባቢዎችን ፣ በተለይም በዳንሻ ግንባር ያለውን የሕወኃት ኃይል በመደምሰስ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት አካባቢውን እንደተቆጣጠረም በመግለጫቸው ወቅት ተናግረዋል፡፡ እንደ አስፈላጊነቱ በሁሉም አቅጣጫ እርምጃው እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡
የትግራይ ክልል ር/መስተዳድር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል ትናንት ጥቅምት 26 ቀን 2013 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ የሕወሓት ኃይል በሰሜን እዝ የሚገኘውን የጦር መሳሪያ ተቆጣጥሮ መታጠቁን እና ለውጊያ በሙሉ አቅም ዝግጁ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
“ከቅርብም ከሩቅም የሚመጣውን ጠላት የመመከት ሙሉ ቁመና ላይ እንደሚገኝም” ርዕሰ መስተዳድሩ አንስተዋል፡፡
የተለያዩ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውጥረቱ እንዲረግብ እና ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ቢጠይቁም የፌዴራል እና የሕወሓት ኃይል ውጊያቸውን ቀጥለዋል፡፡