በአየርላንድ ደብሊን አድርገው ወደ አሜሪካ ዋሽንግተን የሚያቀኑት ሉሲዎቹ ትናንት ማታ ተሸኝተዋል
ለ6ኛ ጊዜ የሚበሩት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሴት የበረራ ቡድን አባላት ወደ ዋሽንግተን አቅንተዋል
ሉሲ በኢትዮጵያ ያልተለመደ ስም አይደለም፡፡ የእናትነት ወላጅነት የአብራክ ክፋይነትም ማመላከቻ ከሆነው ከዚህ ስም የተቀዱ፤ በብዙሃኑ ዘንድ ጎልተው የሚታወቁ ስያሜዎችም አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን በዚህ ቀዳሚ ተጠቃሽ ነው፡፡ ስሙን በማንገብና በማስተዋወቅም ብዙ አበርክቷል፡፡
ስያሜውን ተውሶ ለሉሲ አብራክ ክፋዮች የሰጠው የኢትዮጵያ አየር መንገድም ታሪክን እንደቀደሙ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ታሪክን አድምቀው የሚጽፉ “ሉሲዎች”ን ፈጥሯል፡፡ በአየቪዬሽን ዘርፉ ለመንገስ የሚችሉ ሉሲዎችንም አፍርቷል፡፡
እነዚህ ያለፉትን አምስት አመታት ደመና በሚገማሸርበት ሰማይ በልዕልና ለመንገስ የቻሉ “ሉሲዎች“ም ትናንት ለ6ኛ ጊዜ እንደለመዱት ሁሉ ጨለማ በተጫነው ሰማይ ላይ ነግሰዋል፡፡ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በዓልን ታሳቢ አድርገውም የሶስት አህጉራትን ሰማይ አቋርጠዋል፡፡የአፍሪካ፣የአውሮፓ እና አሜሪካ ሰማይም በእነዚሁ ታሪክ ሰሪ ኢትዮጵያውያን እንስት የበረራ ቡድን አባላት ቁጥጥር ስርም ወድቋል፡፡
ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን ለመዘከርና ለሉሲዎቹ በረራ ሽኝት ለማድረግ ራሱ በአየር መንገዱ ስካይ ላይት ሆቴል በተዘጋጀ ስነ ስርዓት ላይ ንግግርን ያደረጉት ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ ተወልደ ገብረማርያም ሶስት አህጉራትን የሚያቋርጠውና መዳረሻውን አሜሪካ ዋሽንግተን ያደረገው የሉሲዎቹ በረራ በእንስት የአየር መንገዱ የበረራ ቡድን አባላት ብቻ እንደሚፈጸም ገልጸዋል፡፡
የበረራውን አጠቃላይ ሁኔታ፣የጭነቱን፣የመስተንግዶውን፣የቴክኒክና ተያያዥ የደህንነት ጉዳዮችንም የሚቆጣጠረው ይሄው አየርላንድ ደብሊን አርፎ ወደ ዋሽንግተን የሚያቀናው የሉሲዎቹ ቡድን እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ቡድኑን የሚመሩትም የአየር መንገዱ የስራ አስፈጻሚ አባል እና የግብይት ምክትል ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ራሄል ናቸው፡፡
ከ6 ዓመታት በፊት ቀኑን ታሳቢ በማድረግ በሴቶች ብቻ የሚመራ በረራ መደረጉን ያስታወሱት ስራ አስፈጻሚው በአየር መንገዱ ሴቶች በእኩልነት ይሰራሉ ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ 24 ሴት አብራሪሮች እንዲሁም 150 ሴት የአውሮፕላን ቴክኒሺያኖች አሉት፡፡
በመስተንግዶ እና በሌሎችም የምህንድስና እና የቢዝነስ ዘርፎች የተሰማሩ በርካታ ሴት ባለሙያዎችም በአየር መንገዱ ይገኛሉ፡፡
ከተቀጣሪዎቹ 40 በመቶ ያህሉም ሴቶች ናቸው፡፡ ቀሪውን 10 በመቶ በመሙላት የጾታ ተዋጽኦውን እኩል ለማድረግ እንደሚሰራም ነው አቶ ተወልደ የተናገሩት፡፡
የሴት አብራሪዎችን ቁጥር ለማበራከት እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡
በስነ ስርዓቱ በክብር እንግድነት የተገኙት ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴም ታዳሚውን ያነቃቃ ንግግርን አድርገዋል፡፡
”የእኔ እዚህ መገኘት የሴቶች ጉዳይ ከአሁን በኋላ ወደ ኋላ እንደማይመለስ ማሳያ ነው“ ሲሉም ተናግረዋል፡፡
“የሴቶች ቀን የሴቶች መብት መከበር ማለት ነው” ሲሉ ባስደመጡት ንግግርም በየትኛውም የስራም ይሁን የኃላፊነት ቦታ ይኸው መሆን እንዳለበትና እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡
የሴቶች ጉዳይ የሴቶች ብቻ ለእነሱው ብቻ የሚተው ባለመሆኑም ሁሉም በጋራ ሊሰራ ይገባልም ነው ያሉት፡፡
ሴቶች እንዲማሩና ዩኒቨርስቲዎች ለሴቶች የሚመቹና የሚያድጉባቸው መሆን እንዳለባቸውም አስቀምጠዋል፡፡
ሉሲዎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ባንኮክ ነው በ2007 ዓ/ም የበረሩት፡፡ ከዛ ወዲህ ባሉት ተከታታይ ዓመታትም ወደ ኪጋሊ፣ሌጎስ፣ቦነስ አይረስ እና ኦስሎ በረዋል፡፡