“መተከል የምድራችን የጭካኔዎች ጥግ ማሳያ ሆኖ ይታያል“ አቶ ደመቀ መኮንን
በኢትዮጵያ “አረመኔያዊ ድርጊቶች በአብዛኛው በተማሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚቀነባበሩ“ ስለመሆናቸው አቶ ደመቀ ገልጸዋል
ም/ጠ/ሚኒስትርና የውጭ ጉ/ሚ አቶ ደመቀ ቻግኒ ተገኝተው ከመተከል ተፈናቃዮች ጋር ተወያይተዋል
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና የገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌው ያሉበት ቡድን የመተከል ተፈናቃዮችን ቻግኒ ተገኝተው ጎብኝተዋል፡፡
አቶ ደመቀ መኮንን ከመተከል የተፈናቀሉ እና በቻግኒ ራንች የተባለ መጠለያ ጣቢያ ከተጠለሉ ተጎጂዎች ጋር የተወያዩ ሲሆን ተፈናቃዮቹ መንግሥት ዘላቂ መፍትሔ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ጠይቀዋል።
የዕለት ደራሽ የምግብ፣ አልባሳት እና የመጠጥ ውኃ ተደራሽነት ችግሮች በመኖራቸው እናቶች እና ሕፃናት ችግር ላይ መሆናቸውንም ተጎጂዎቹ መናገራቸውን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡
ም/ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን “ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ፈጻሚዎች በደሃ ደም ላይ ተረማምደዋል፤ ግን ከተጠያቂነት ማምለጥ አይችሉም“ ሲሉ በኢንጂባራ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ምረቃ ስነ ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል፡፡
መተከል የአብሮነት ማሳያና የኢትዮጵያ ተስፋ የነበረ አካባቢ የነበረ ቢሆንም “አሁን ግን በከፋ ጫፍ ፣ በምድር ላይ የጭካኔዎች ጥግ ማሳያ ሆኖ እንደሚታይ” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ አቶ ደመቀ ጥቂት ሰዎች ከሀገር እና ከሕዝብ በላይ ሆነው በሀገር ላይ የከፋ ክህደት እና ጭካኔ ስለማሳየታቸውም ነው ያነሱት፡፡ ሚኒስትሩ በንግግራቸው በመተከል አካባቢ “ዜጋን በማንነቱ እየለዩ በመጨፍጨፍ ጭካኔና ጭፍጨፋን የእርካታ ምንጫቸው ያደረጉ አካላት አሉ” ብለዋል፡፡
በዚህም ሀገር የማትጠብቀው ጉድለትና ጥፋት ሲስተዋል መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጸሙት “አረመኔያዊ ድርጊቶች በአብዛኛው በተማሩና የተሻለ ግንዛቤ አላቸው ተብሎ በሚጠበቁ የሕብረተሰብ ክፍሎች ፊታውራሪነት እየተቀነባበሩና እየተፈጸሙ” መሆኑን የገለጹት አቶ ደመቀ ፣ ሕዝቡ ግን የአብሮነት ባህሉን ጠብቆ ይህንን ችግር ለመሻገር ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል፡፡
እነዚህ የሀገር እና የሕዝብ ጠላቶች በአሁኑ ወቅት በተባበረ ክንድ እየተወገዱ ቢሆንም ለዘመናት ሲያራምዱት የነበረው የተሳሳተ ትርክት ፈጽሞ ከስሩ እስኪነቀል ድረስ በአብሮነት ልንታገለው፣ ልናርመው እና ልናስተካክለው ይገባል” ብለዋል ም/ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በተለያዩ ጌዜያት በግፍ በተፈጸመ ጭፍጨፋ በርካታ ንጹኃን ይወታቸውን ማጣታቸው ይታወቃል፡፡