የአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባዔ ኬቨን ማካርቲ ከሃላፊነታቸው ተነሱ
ሪፐብሊካኑ ማካርቲ በራሳቸው ፓርቲ አባላት ድምጽ ተነፍገው ከስልጣን የተነሱ የመጀመሪያው የአሜሪካ ተወካዮች ምክርቤት አፈጉባኤ ሆነዋል
አፈጉባኤው ዋይትሃውስ ለዩክሬን ድጋፉን እንዲቀጥል ሚስጢራዊ ንግግር አድርገዋል የሚል ወቀሳ ቀርቦባቸዋል
የአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባዔ ኬቨን ማካርቲ ከሃላፊነታቸው ተነሱ።
በምክር ቤቱ ፍርሎሪዳን የወከሉት ሪፐብሊካኑ ማት ጌትዝ አፈጉባኤው ከስልጣናቸው እንዲነሱ ያቀረቡት ጥያቄ በ216 ድጋፍና 210 ተቃውሞ ጸድቋል።
435 መቀመጫ ባለው ምክርቤት ሪፐብሊካኖች የዘጠኝ መቀመጫ ብልጫ ያላቸው ሲሆን፥ አፈጉባኤውን ከመነሳት ለመታደግ ከአምስት በላይ ሪፐብሊካኖች ድምጽ መስጠት አልነበረባቸውም።
ይሁን እንጂ ስምንት ሪፐብሊካኖች ከዴሞክራቶች (208) ጋር ተደምረው ማካርቲ እንዲነሱ ድምጽ መስጠታቸውን ነው ሬውተርስ የዘገበው።
በዚህም ኬቨን ማካርቲ በአሜሪካ ታሪክ በራሳቸው ፓርቲ ከሃላፊነታቸው የተነሱ የመጀመሪያው አፈጉባኤ ሆነዋል።
ማካርቲ የአሜሪካ የመንግስት መስሪያ ቤቶችን በከፊል ከመዘጋት የሚታደግ ስምምነት ከህግ መወሰኛ ምክር ቤት ወይም ሴኔቱ ጋር መፈራረማቸው በወግ አጥባዊ ሪፐብሊካኖች ተቃውሞ አስነስቶባቸዋል።
የፍሎሪዳው የሪፐብሊካን ተወካይ ማት ጌትዝ አፈጉባኤው ከዋይትሃውስ ጋር ለዩክሬን የሚደረገው ድጋፍ ስለሚቀጥልበት ሁኔታ ሚስጢራዊ ምክክር ማድረጋቸውን ይጠቅሳሉ።
ከሃላፊነታቸው የተነሱት ኬቨን ማካርቲ ግን ውንጀላውን አይቀበሉትም፤ ማት ጌትዝ “እይታን ለማግኘት የፈጠረውና ግላዊ ልዩነትን ወደ አደባባይ ያወጣበት ነው” ብለዋል።
“ለማምንበት ነገር ታግያለሁ” የሚሉት ማካርቲ በድጋሚ አፈጉባኤ ለመሆን እንደማይፎካከሩ ገልጸዋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊ መሆናቸው የሚነገርላቸው ማካርቲ በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ላይ ክስ ለመመስረት ምርመራ እንዲከፈት ማዘዛቸው በዴሞክራቶች ዘንድ ሲያስወቅሳቸው ቆይቷል።
ቢያንስ ለአንድ ሳምንት ያለአፈጉባኤ የሚቆየው የአሜሪካ የተወካዮች ምክርቤት በቀጣይ ማንን አፈጉባኤ አድርጎ እንደሚመርጥ አልታወቀም።
የሪፐብሊካን ፓርቲ ህግ አውጪዎች ከስድስት ቀናት በኋላ ተገናኝተው ቀጣዩን አፈጉባኤ ለመምረጥ ቀጠሮ ስለመያዛቸው አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።