የሃውቲ ታጣቂዎች በእስራኤል ላይ የድሮንና ሚሳኤል ጥቃት መፈጸማችውን ገለጹ
በኢራን የሚደገፈው ቡድን ሶስተኛውን ጥቃት ማድረሱንና ከፍልስጤማውያን ጎን እንደሚሰለፍ አስታውቋል
እስራኤል የየመኑን ታጣቂ ቡድን ጥቃት አልታገስም ብትልም የደረሰውን ጉዳት አልጠቀሰችም
የየመኑ ታጣቂ ቡድን ሃውቲ ከመቀመጫው ሰንአ ወደ እስራኤል የሚሳኤል እና ድሮን ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።
ሃማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ከከፈተ አንስቶ ድጋፉን የገለጸው ቡድኑ በእስራኤል ላይ ሶስተኛውን የባለስቲክ ሚሳኤል ጥቃት ማድረሱን ነው የገለጸው።
የቡድኑ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሬ “በርካታ ቁጥር ያላቸው ባለስቲክ ሚሳኤሎችን ወደ እስራኤል ተኩሰናል፤ ፍልስጤማውያን ድል እስኪያደርጉ ድረስ ጥቃታችን ይቀጥላል” ብሏል።
ሃውቲ ከአራት ቀናት በፊት በግብጽ የደረሰውን የድሮን ጥቃት መፈጸሙ የተነገረ ሲሆን፥ ወደ እስራኤል የተተኮሱ ሶስት የክሩዝ ሚሳኤሎቹም በአሜሪካ ባህር ሃይል ተመተው መውደቃቸው አይዘነጋም።
የእስራኤል ብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ዛቺ ሃኔግቢ ሀገራቸው የሃውቲ ጥቃትን እንደማትታገስ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ቴል አቪቭ ለየመኑ ቡድን ምን አይነት ምላሽ እንደምትሰጥ አላብራሩም።
የሚሳኤል እና ድሮን ቴክኖሎጂ አቅሙ በቴህራን ድጋፍ መጎልበቱ የሚነገርለት ሃውቲ ፍልስጤማውያንን ከእስራኤል ጥቃት ለመታደግ የሚወስደውን እርምጃ እንደሚያጠናክር ገልጿል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆሴን አሚርአብዶላሂያን ትናንት በሰጡት መግለጫም የቴህራን አጋሮች የሚወስዱት እርምጃ ከዚህም የበለጠ እንደሚሆን ተናግረዋል።
“የኢራን አጋሮች የማንንም ምክር አይጠብቁም፤ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ ከወጣ የትኛውም አካል ከችግር አያመልጥም” ሲሉም ተደምጠዋል።
የሃውቲ ሚሳኤሎች እና ድሮኖች እስራኤል ለመድረስ የሳኡዲ እና ዮርዳኖስ አየርን ማቋረጣቸው ግድ መሆኑ ሪያድን አሳሳቢ ሆኖባታል።
በቻይና አደራዳሪነት ግንኙነታቸውን ለማደስ የተስማሙት ኢራን እና ሳኡዲ አረቢያ በሃውቲ ጥቃት ምክንያት ግንኙነታቸው መሻከር እንዳይጀምር ተሰግቷል።
ቴል አቪቭ ለሃውቲ የባለስቲክ ሚሳኤል እና ድሮን ጥቃት የምትሰጠው ምላሽም ሪያድን የሚነካ ከሆነ ጦርነቱ አድማሱን ሊያሰፋ እንደሚችል ነው እየተነገረ ያለው።