የየመኑ ሃውቲ በእስራኤል የሃይል ማመንጫ ጣቢያ ላይ የሚሳኤል ጥቃት ፈጸሜያለሁ አለ
በደቡባዊ ሃይፋ የሚገኘው የኦሮት ራቢን ሃይል ማመንጫ ጣቢያ "ፍልስጤም 2" በተሰኘው ባለስቲክ ሚሳኤል መመታቱንም አስታውቋል
የእስራኤል ጦር በበኩሉ የሃውቲዎችን ሚሳኤል መትቶ መጣሉን ገልጿል
የየመኑ ሃውቲ በእስራኤል የሃይል ማመንጫ ጣቢያ ላይ የሚሳኤል ጥቃት መፈጸሙን አስታወቀ።
የቡድኑ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሬ በዛሬው እለት በአል ሚስራህ ቴሌቪዥን በተላለፈ መግለጫቸው "በደቡባዊ ሃይፋ በሚገኘው የኦሮት ራቢን ሃይል ማመንጫ ጣቢያ ላይ የሚሳኤል ጥቃት ፈጽመናል" ብለዋል።
ቃል አቀባዩ ጥቃቱ የተፈጸመው "ፍልስጤም - 2" በተሰኘ ባለስቲክ ሚሳኤል መሆኑንም አብራርተዋል።
ሳሬ "ኢላማችን ግቡን መቷል" ቢሉም ስለደረሰው ጉዳት ዝርዝር አስተያየት አልሰጡም ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
የእስራኤል ጦር በበኩሉ የሃውቲዎች ሚሳኤል ወደ እስራኤል የአየር ክልል ከመግባቱ በፊት በአየር መቃወሚያ ተመቶ መውደቁን በመጥቀስ የቡድኑ ቃል አቀባይ የሰጡትን መግለጫ ውድቅ አድርጓል።
የሃውቲዎች ቃል አቀባይ ያህያ ሳሬ በመግለጫቸው ቡድኑ "ለተጨቆኑ ፍልስጤማውያን የመድረስ ሃይማኖታዊ፣ ሞራላዊ እና ሰብአዊ ግዴታውን መወጣቱን ይቀጥላል" ሲሉ ተደምጠዋል።
በኢራን እንደሚደገፍ የሚነገርለት ሃውቲ እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመውን "የዘር ማጥፋት" ለማስቆም የራሱን ሃይል እያደረጀ በቴል አቪቭ ላይ መሰል ጥቃቶችን ማድረሱን እንደሚቀጥልም ነው የተናገሩት።
እስራኤል ከወደ የመን የሚቃጣባትን የሚሳኤል ጥቃት ለመመከት አሜሪካ ሰራሹን "ታድ" የሚሳኤል መቃወሚያ ስርአት በቅርቡ መጠቀም ጀምራለች።
መቃወሚያው ባለፈው ሳምንትም ከሃውቲዎች የተተኮሰ ሚሳኤልን መትቶ መጣሉን መግለጿ ይታወሳል።
ሃውቲዎች ግን የአሜሪካው "ታድ" መቃወሚያን ጥሰው የሚያልፉ ባለስቲክ ሚሳኤሎች መታጠቃቸውን በመጥቀስ ጥቃታቸው እንደሚቀጥል በመዛት ላይ ናቸው።
ከ45 ሺህ 700 በላይ ፍልስጤማውያንን ህይወት የቀጠፈውን ጦርነት የሚቃወመውና ለፍልስጤማውያን አጋርነቱን የሚገልጸው ሃውቲ እስራኤል በጋዛ ጦርነት ከጀመረች ጀምሮ በቀይ ባህር በሚጓዙ መርከቦች ላይም የሚሳኤልና ድሮን ጥቃት ሲፈጽም መቆየቱ ይታወሳል።
እስራኤልና አጋሯ አሜሪካም በየመን የቡድኑ ይዞታዎች ላይ ተደጋጋሚ የአየር ድብደባዎችን መፈጸማቸው ይታወቃል።