እስራኤል በየመን የሃውቲ ይዞታዎችን በ14 ጄቶች ደበደበች
ሃውቲዎች ሁለት "ፍልስጤም" የተሰኙ ባለስቲክ ሚሳኤሎችን ከተኮሱ በኋላ ነው ቴል አቪቭ በየመን መጠነ ሰፊ የአየር ጥቃት የፈጸመችው
የየመኑ ቡድን የጋዛው ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ከ200 በላይ ሚሳኤሎችን ወደ እስራኤል ተኩሷል
እስራኤል በየመን የሃውቲ ይዞታዎች ላይ ከፍተኛ ድብደባ መፈጸሟን አስታወቀች።
በ14 ጄቶች ተፈጽሟል በተባለው ጥቃት በጥቂቱ የዘጠኝ ሰዎች ህይወት ማለፉን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
በመጀመሪያው ዙር ጥቃት በሆዴይዳህ ወደብ የሚገኙ የሃውቲ መሰረተ ልማቶች፣ የሳሊፍ እና ራስ ኢሳ የነዳጅ ማከማቻዎች ኢላማ መሆናቸውን የእስራኤል ጦር ገልጿል።
በሁለተኛው ዙር ድብደባ ደግሞ በሰንአ የሚገኝ የሃውቲዎች የኢነርጂ መሰረተ ልማት መመታቱን ነው ጦሩ ያስታወቀው።
አል ሚስራህ የተሰኘው ሃውቲዎች የሚያስተዳድሩት የቴሌቪዥን ጣቢያ የተወሰኑት የአየር ጥቃቶች የኤሌክትሪክ ሃይል ጣቢያዎችን ኢላማ በማድረጋቸው የሰንአን የሃይል ቀውስ ውስጥ ያባብሰዋል ብሏል።
መሀመድ አል ባሻ የተባለ የየመን ጉዳይ ተንታኝ በጥቃቱ ከሰንአ ሱቆች፣ መደብሮች እና የንግድ ተቋማት ውስጥ ቢያንስ ሩቡ ከኤሌክትሪክ ሀይል ውጭ እንደሚሆኑ ተናግሯል።
የእስራኤል ጦር በፈጸመው መጠነሰፊ ጥቃት ስለተገደሉ የመናውያንም ሆነ ስለደረሰው ዝርዝር ጉዳት ያለው ነገር የለም።
የመከላከያ ሚኒስትሩ እስራኤል ካትዝ፥ "ሃውቲዎች በእስራኤል ላይ እጁን የሚሰነዝር እጁ እንደሚቆረጥ ሁሌም ማስታወስ አለባቸው፤ እኛን የሚጎዳ በብዙ እጥፍ የእጁን ያገኛል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በሃውቲዎች ቁጥጥር ስር ያለችውና ከሰንአ በ145 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ሆዴይዳህ ለየመናውያን አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ የሚገባባት ቁልፍ ወደብ ናት።
ሃውቲዎች ከኢራን የጦር መሳሪያዎችን የሚያስገቡት በዚሁ ወደብ ነው የምትለው እስራኤል በሆዴይዳህ ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ፈጽማለች።
የዛሬው ጥቃት የተፈጸመው ከየመን ወደ እስራኤል ሚሳኤሎች ከተተኮሱ በኋላ ነው። ሚሳኤሎቹ የእስራኤልን ግዛት ሳይሻገሩ ተመተው መውደቃቸውን የገለጸው የእስራኤል ጦር፥ በየመን የተፈጸመው ድብደባ አስቀድሞ የታሰበበት እንጂ ለዛሬው የሃውቲዎች ጥቃት አጻፋ አይደለም ብሏል።
የሃውቲ ታጣቂ ቡድን ቃል አቀባይ ያህሳ ሳሬ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት ሁለት "ፍልስጤም" የተሰኙትን ባለስቲክ ሚሳኤሎች ወደ እስራኤል ተኩሰናል ብለዋል።
እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመውን ድብደባ እንድታቆም የሚጠይቀውና የፍልስጤማውያን አጋር ነኝ የሚለው የየመኑ ቡድን ከጥቅምት 2023 ወዲህ ከ200 በላይ ሚሳኤሎች እና ድሮኖችን ወደ እስራኤል መተኮሱ ተገልጿል።
የኔታንያሁ አስተዳደርም የሃውቲዎች ድሮን በቴል አቪቭ የአንድ እስራኤላዊ ህይወትን ከቀጠፈችና ከ10 በላዩን ካቆሰለች በኋላ በሀምሌ ወር ሆዴይዳህ ላይ ከፍተኛ ድብደባ መፈጸሟ ይታወሳል።
ኔታንያሁ በመስከረም 2024 ከአሜሪካ ሲመለሱ ሃውቲዎች በቤን ጉሪን አውሮፕላን ማረፊን ኢላማ ያደረገ ሚሳኤል መተኮሳቸውን ተከትሎም እስራኤል የየመናውያን እስትንፋስ የሆነውን ወደብ በድጋሚ መደብደቧ አይዘነጋም።