የሀውቲ ታጣቂዎች በአሜሪካ እና በዩኬ መርከቦች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን አስታወቁ
የአሜሪካ ማዕከላዊ እዝ በትናንትናው እለት አሜሪካ በወሰደችው ራስን የመከላከል እርምጃ ሁለት የሀውቲ የድሮችን መትቻለሁ ብሏል
የሀውቲ ቃል አቀባዩ በአሜሪካ እና ዩኬ መርከቦች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ይቀጥላል ሲል ተናግሯል
የሀውቲ ታጣቂዎች በአሜሪካ እና በዩኬ መርከቦች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን አስታወቁ።
የሀውቲ ታጣቂዎች በሁለት የአሜሪካ እና የዩናይትድ ኪንግደም(ዩኬ) መርከቦች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን የሀውቲ ጦር ቃል አቀባይ ማስታወቁን ሲጂቲኤን ዘግቧል።
ቃል አቀባዩ ያህያ ሳሪአ "በቀይ ባህር ላይ ሁለት ወታደራዊ ጥቃቶችን ፈጽመናል፤ አንደኛው ጥቃት 'ስታር ናሲያ' በተባለችው የአሜሪካ መርከብ ላይ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ 'ሞርኒንግ ታይድ' በተባለች የዩኬ መርከብ ላይ ነው" ብሏል።
እንደቃል አቀባዩ ከሆነ ሁለቱም መርከቦች በናቫል ሚሳይል ቀጥትኛ እና ትክክለኛ ጥቃት ደርሶባቸዋል።
ጥቃቱን የፈጸሙት ለፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማሰ አጋርነት ለማሳየት መሆኑን የገለጸው ቃል አቀባዩ በአሜሪካ እና ዩኬ መርከቦች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ይቀጥላል ብሏል።
ከሰአታት በፊት የዩኬ የማሪታይም ትሬድ ኦርጋናይዜሽን የዩኬ መርከብ በሀውቲ ቁጥጥር ስር ካለው ሆዲህ ወደብ አቅራቢያ በሚሳይል መመታቷን የሚያሳይ ሪፖርት መቀበሉን ገልጾ ነበር።
ድርጁቱ መርከቧ መካከለኛ የሚባል ጉዳት እንደደረሰባት እና አሁንም እየተጓዘች መሆኑን ጠቅሷል።
የአሜሪካ ማዕከላዊ እዝ በትናንትናው እለት አሜሪካ በወሰደችው ራስን የመከላከል እርምጃ ሁለት የሀውቲ የድሮችን መትቻለሁ ብሏል።
አሜሪካ እንደገለጸችው እነዚህን ሁለት ድሮኖች በሀውቲ ቁጥጥር ስር ባሉ ቦታዎች ዘመለየት ጥቃት ሳያደርሱ አስቀድማ እርምጃ ወስዳባቸዋለች።
በቀይ ባህር ያለውን የመርከቦች እንቅስቃሴ ሰላማዊ አደርጋለሁ የምትለው አሜሪካ፣ በሀውቲ ታጣቂዎች ይዞታ ላይ አጋሮቿን በማሳተፍ ጥቃት እያደረሰች ትገኛለች።