የሀውቲ ቃል አቀባይ አዲሱ ጥቃት ጥብቅ፣ ጠንካራ እና ውጤታማ ምላሽ ይኖረዋል ሲል ተናግሯል
የየመን ሀውቲ ታጣቂዎች በአሜሪካ ላይ አጸፋ ምላሽ እንሰጣለን ሲሉ ዝተዋል።
ታጣቂዎቹ ይህን ዛቻ ያሰሙት አሜሪካ በየመን ውስጥ በድጋሚ የአየር ጥቃት መሰንዘሯን ተከትሎ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
የቀይ ባህር ቀጣና የመርከብ እንቅስቃሴ እጠብቃለሁ የምትለው አሜሪካ ባለፈው 24 ሰአታት ውስጥ በድጋሚ በየመን ውስጥ የአየር ድብደባ በማድረሷ የተቆጡት ሀውቲዎች "ጠንካራ ውጤታማ" ምላሽ እንሰጣለን ሲሉ ዝተዋል።
ጥቃቱ የእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ወደመካከለኛው ምስራቅ የተስፋፋውን ግጭት የበለጠ ያባብሰዋል የሚው ስጋት እንጨምር አድርጓል።
አሜሪካ እና ዩኬ በየመን የሀውቲ ታጣቂዎች ይዞታ ላይ በደርዘን የሚቆጠር የአየር ድብደባ ካደረሱ ከአንድ ቀን በኋላ በደረሰው አዲስ ጥቃት ራዳር መምታቷን አሜሪካ ገልጻለች።
የሀውቲ ቃል አቀባይ አዲሱ ጥቃት ጥብቅ፣ ጠንካራ እና ውጤታማ ምላሽ ይኖረዋል ሲል ተናግሯል።
ቱርክ፣ አሜሪካ እና ዩኬ በየመን ላይ ያደረሱትን ጥቃት ተቃውማለች።
የቱርኩ ፕሬዝደንት ጣይብ ኢርዶጋን አሜሪካ እና ዩኬ ቀይ ባህርን ወደ ደም ባህር ለመቀየር እየሞከሩ ነው በማለት ነበር ጠንካራ ትችት የሰነዘሩት።
አሜሪካ እና ዩኬ በየመን ጥቃት የሰነዘሩት ሀውቲዎች በየቀይ ባህር የመርከብ መስመር ላይ ጥቃት በማድረሳቸው ነው ቢሉም፣ ኢርዶጋን ምላሹ ተመጣጣኝ አይደለም ብለዋል።
ሩሲያ ሁለቱ ሀገራት በየመን በመፈጸሙት ጉዳይ ምክክር እንዲደረግ የተመድ የጸጥታው ምክርቤት እንዲሰበሰብ ጠይቃለች።