እስራኤል ወደ ጋዛ የትኛውም ሰብአዊ ድጋፍ እንዳይገባ አገደች
ሃማስ በአሜሪካ የቀረበውን የተኩስ አቁም ማራዘሚያ እቅድ የማይቀበል ከሆነም "የከፋ ችግር ይከሰታል" ስትል አስጠንቅቃለች

የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን በበኩሉ የእስራኤልን የተኩስ አቁም የማራዘም ሃሳብ "ተራ ማወናበጃ" ነው ብሎታል
እስራኤል ወደ ጋዛ የትኛውም ሰብአዊ ድጋፍ እንዳይገባ ማገዷን አስታወቀች።
የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከጥቂት ሰአት በፊት ባወጣው መግለጫ ሃማስ ትናንት እኩለ ለሊት ላይ የተጠናቀቀውን የመጀመሪያ ምዕራፍ ተኩስ አቁም ለማራዘም ፈቃደኛ ባለመሆኑ ከዛሬ ጀምሮ ወደ ጋዛ ሰብአዊ ድጋፍ አይገባም ብሏል።
እስራኤል በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመካከለኛው ምስራቅ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ የቀረበውን የተኩስ አቁም ማራዘሚያ ምክረሃሳብ ተቀብላ ስምምነቱ በጊዜያዊነት ለ42 ቀናት እንዲራዘም መስማማቷን መግለጿ ይታወሳል።
የፍልስጤሙ ሃማስ ቃል አቀባይ ግን የተኩስ አቁም ማራዘሚያው "ተራ ማወናበጃ" ነው ያሉ ሲሆን፥ አደራዳሪዎቹ እስራኤል ወደ ጋዛ ሰብአዊ ድጋፍ እንዳይገባ ያሳለፈችውን ውሳኔ እንድትቀለብስ ጫና እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
ሃማስ አስቀድሞ ሁለተኛው ምዕራፍ ተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ድርድር መጀመር አለበት እንጂ ተኩስ አቁሙን በ42 ቀናት ማራዘም ተቀባይነት የለውም ማለቱን ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል።
በአሜሪካ፣ ግብጽ እና ኳታር አደራዳሪነት በጥር 19 2025 የተደረሰው ስምምነት ሶስት ምዕራፎች ያሉት ሲሆን፥ እስራኤል በሁለተኛው ምዕራፍ ከጋዛ ወታደሮቿን ሙሉ በሙሉ እንድታስወጣ የሚያስችል ስምምነት የመጀመሪያው ምዕራፍ ከመጠናቀቁ በፊት መደረስ እንዳለበት ያመላክታል።
በኳታር መዲና ዶሃ በሁለተኛው ምዕራፍ ተኩስ አቁም ዙሪያ ሊደረግ የነበረው ድርድር ሳይሳካ ቀርቷል፤ ከሰሞኑም በካይሮ የተካሄደው ስብሰባ ያለስምምነት ተጠናቋል።
እስራኤል በአሜሪካው ፕሬዝዳንት የመካከለኛው ምስራቅ ልዩ መልዕክተኛ የቀረበውን ጊዜያዊ የተኩስ ማቆም ማራዘሚያ ብትቀበለውም ሃማስ ውድቅ ስላደረገው ተፈጻሚነቱ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።
የኔታንያሁ ጽህፈት ቤት በመግለጫው "እስራኤል ታጋቾች የማይለቀቁበትን ተኩስ አቁም አትፈቅድም፤ ሃማስ በእምቢታው ከጸና የከፋ ችግር ይከሰታል" ሲል አስጠንቅቋል። በአሁኑ ወቅት በጋዛ 59 ታጋቾች እንደሚገኙ የተነገረ ሲሆን፥ ከነዚህ ውስጥ 24ቱ በህይወት ያሉ ናቸው ተብሏል።
ሃማስ በቀጣይ ስድስት ሳምንታት አቋሙን ከለወጠ ግን እስራኤል ወደ ድርድር ለመመለስ ዝግጁ መሆኗን የጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።
ሁለተኛው ምዕራፍ የተኩስ አቁም ድርድር የማይሳካ ከሆነ እስራኤል ከ42 ቀናት በኋላ በጋዛ ዳግም ጦርነት ልትጀምር እንደምትችል ተገልጿል።
ከ48 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን ህይወት የቀጠፈው ጦርነት ከ2 ሚሊየን በላይ ፍልስጤማውያን የእለት ደራሽ ድጋፍ ጠባቂ አድርጓል።
በመጀመሪያው ምዕራፍ የተኩስ አቁም በየእለቱ 600 እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ እንዲገቡ ቢደረግም ከፍላጎቱ አንጻር አነስተኛ መሆኑን አለማቀፍ የረድኤት ተቋማት ሲገልጹ ቆይተዋል።
ሃማስ እና እስራኤል የተኩስ አቁም ሰጣ ገባቸው ቀጥሎ እስራኤል ወደ ጋዛ እርዳታ እንዳይገባ ካገደች የፍልስጤማውያን ሰብአዊ ቀውስ አሳሳቢ ደረጃ ይደርሳል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።