የየመን ሀውቲ ታጣቂዎች በአሜሪካ የጦር መርከብ ላይ ጥቃት አደረሱ
ጥቃቱ የተፈጸመው አሜሪካ ማዕከላዊ እዝ በሀውቲ የጦር መሳሪያ ማከማቻ ላይ በተከታታይ የአየር ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ ነው
የሀውቲ ታጣቂዎች በበርካታ ሚሳይሎች በአሜሪካ የጦር መርከቦች ላይ የፈጸሙትን ጥቃት ማክሸፉን የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ፔንታጐን አስታውቋል
የየመን ሀውቲ ታጣቂዎች በአሜሪካ የጦር መርከብ ላይ ጥቃት አደረሱ።
የሀውቲ ታጣቂዎች በበርካታ ሚሳይሎች በአሜሪካ የጦር መርከቦች ላይ የፈጸሙትን ጥቃት ማክሸፉን የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ፔንታጐን አስታውቋል።
ባለፈው ሰኞ ቢያንስ ስምንት ድሮኖች፣ አምስት ጸረ-መርከብ ባለስቲክ ሚሳይሎች እና ሶስት ጸረ-መርከብ ክሩዝ ሚሳይሎች ዩኤስኤስ ስቶክዳሌ እና ዩኤስኤስ ስፑራንስን ኢላማ አድርገው ነበር ተብሏል።
የፔንታጎን የፕሬስ ኃላፊ ሜጀር ጀነራል ፓት ራይደር መርከቦቹ የተተኮሱትን ሚሳይሎች ማክሸፋቸውን እና በሰውም ሆነ በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን በትናንትናው እለት ተናግረዋል።
ጥቃቱ የተፈጸመው አሜሪካ ማዕከላዊ እዝ በሀውቲ የጦር መሳሪያ ማከማቻ ላይ በተከታታይ የአየር ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ ነው።
ሮይተርስ በየመኑ የሀውቲ ታጣቂ ቡድን የሚመራውን አል ማሲራህ ቴሌቪዥንን ጠቅሶ እንደዘገበው በሁለት ተከታታይ ጥቃቶች ሁለት የአሜሪካ የጦር መርከቦች እና ሌላ በአረቢያን ባህር ላይ ይጓዝ የነበረ መርከብ ኢላማ ተደርገዋል።
የቡድኑ ቃል አቀባይ ያህያ አል ሰርኤ በኤክስ ገጹ ባወጣው መግለጫ ቡድኑ በበርካታ ሚሳይሎች የአሜሪካዋን አብሃም ሊንክለን ኤየርክራፍት ተሻከሚ መርከብ "በተሳካ ሁኔታ" መደብደቡን አስታውቋል።
ራይደር በአብረሃም ሊንክለን መርከብ ላይ ጥቃት መድረሱን እንደማያውቅ ገልጿል።
"ለሀውቲዎች ግልጽ ማድረግ የምንፈልገው ግዴለሽ እና ህገወጥ የሆኑ ጥቃቶች ምላሽ እንዳላቸው ነው።"
ሀውቲዎች በቀጣናው ሄዝቦላን እና ሀማስን ጨምሮ በኢራን የሚደገፈው የታጣቂወች ቡድን አካል ናቸው። ታጣቂዎቹ ከህዳር 2023 ጀምሮ በቀይ ባህር እና በኤደን ባህረ ሰላጤ በሚያልፉ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት እየፈጸሙ ነው። ሁለት መርከቦችን ያሰጠሙ ሲሆን ሌላ አንድ መርከብ ደግሞ በቁጥጥራቸው ስር ማዋላቸው ይታወሳል።
ታጣቂዎቹ ጥቃቱን እየፈጸሙ ያሉት ከእስራኤል ጋር እየተዋጋ ላለው የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ አጋርነት ለማሳየት ነው።
ታጣቂዎቹ ከእስራኤል፣ ዩናይትድ ኪንገደም(ዩኬ) እና ከአሜሪካ ግንኙነት አላቸው የሚሏቸውን መርከቦች ያጠቃሉ። በዚህ አመት መጀመሪያ ላይ አሜሪካ፣ ዩኬ እና ሌሎች 12 ሀገራት በቀይ ባህር የመርከብ መስመርን ለመጠበቅ 'ኦፐሬሽን ፕሮስፔሪቲ ጋርዲያን' የተባለ ዘመቻ ከፍተዋል።
ባለፈው ጥቅምት ወር የአሜሪካ ጦር የመን ውስጥ በ15 የሀውቲ ይዞታዎች ላይ የአየር ጥቃት ፈጽማለች።