አሜሪካ ጥቃቱን አስመልክታ እስካሁን በይፋ ያወጣችው መግለጫ የለም
የየመን ሁቲ አማጺያን የአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን መተው ጣሉ
ከ10 ወራት በፊት ሐማስ በእስራኤል ምድር ድንገተኛ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ ነበር በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት የተቀሰቀሰው፡፡
በጋዛ የተጀመረው ይህ ጦርነት በየጊዜው መልኩን እየቀያየረ ወደ ሊባኖስ እና የመን እየተስፋፋ ሲሆን በቀጣይ ደግሞ በሌሎች አካባቢዎችን ሊሰፋ እንደሚችል ስጋት አይሏል፡፡
አሜሪካ ከእስራኤል ጎን በመቆሟ ከሐማስ ጎን መሆናቸውን የሚገልጹት የየመኑ ሁቲ አማጺ ቡድን ከእስራኤል እና አሜሪካ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ የንግድ መርከቦችን ኢላማ አድርገዋል፡፡
አማጺያኑ ከዚህ በተጨማሪም የሁለቱ ሀገራት ወታደራዊ ጣቢያዎችንም ኢላማ ያደረገ ሲሆን በዛሬው ዕለት ኤኪው-9 የተሰኘ የአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላንን መተው እንደጣሉ አል አረቢያ ዘግቧል፡፡
አል አረቢያ በዘገባው ላይ እንዳለው አማጺያኑ በባሊስቲክ ሚሳኤል አማካኝነት ንብረትነቱ የአሜሪካ የሆነ ሰው አልባ አውሮፕላን መተው ጥለዋል፡፡
የየመን አማጺያን ከዚህ በፊት ሶስት መሰል ሰው አልባ አውሮፕላን መተው መጣላቸውን ከሁለት ወር በፊት ቪኦኤ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
የአሜሪካ ሁለት መርከቦች በየመን አማጺያን መመታታቸው ተገለጸ
ሰዓዳ በተሰኘው የሰሜናዊ የመን ግዛት የተሰነዘረው ይህ ጥቃት እስራኤል ከ15 ቀናት በፊት በሆዴዳህ ወደብ ካደረሰችው ድብደባ በኋላ የመጀመሪያ ነው ተብሏል፡፡
ይሁንና አሜሪካ እስካሁን ስለደረሰው ጥቃት እስካሁን በይፋ ያወጣችው መረጃ የሌለ ሲሆን በአማጺያኑ ተመቶ ወድቋል የተባለው ኤኪው-9 ሰው አልባ አውሮፕላን በሰዎች ተከቦ ሲመለከቱት የሚያሳየው ምስል እየተሰራጨ ይገኛል፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ የተጀመረው ጦርነት ወደ ቀጥታ ጦርነት ሊቀየር ይችላል በሚል በርካታ ሀገራት ዜጎቻቸው ወደ አካባቢው ሀገራት እንዳይጓዙ ከማሳሰብ ባለፈ በሊባኖስ የሚኖሩ ዜጎቻቸው በአስቸኳይ እንዲወጡ አስጠንቅቀዋል፡፡