የሀውቲ ታጣቂዎች የዩኬ መርከቦችን ማስጠም እንቀጥላለን ሲሉ ዛቱ
ሀውቲዎች በቀይ ባህር ላይ በሚያደርሱት ጥቃት በርካታ የንግድ መርከብ ኩባንያዎች አቅጣጫ ለመቀየር ተገድደዋል
ባለፈው ወር በሀውቲ ታጣቂዎች በጸረ-መርከብ ሚሳይል የተመታችው ሩቢማር የተሰኘችው የዩኬ መርከብ ሰጥማለች
የሀውቲ ታጣቂዎች የዩኬ መርከቦችን ማስጠም እንቀጥላለን ሲሉ ዛቱ።
ንብረትነቷ የእንግሊዝ የሆነች መርከብ እንድትሰጥም ያደረጉት የሀውቲ ታጣቂዎች የዩናይትድ ኪንግደም(ዩኬ) መርከቦችን ማስጠማቸውን እንደሚቀጥሉበት ዝተዋል።
የአሜሪካ ጦር ቅዳሜ እለት እንዳረጋገጠው ባለፈው ወር በሀውቲ ታጣቂዎች በጸረ-መርከብ ሚሳይል የተመታችው ሩቢማር የተሰኘችው የዩኬ መርከብ ሰጥማለች።
"የመን ተጨማሪ የዩኬ መርከቦችን ማስጠሟን ትቀጥላለች" ሲል በሀውቲ ታጣቂዎች የሚመራው መንግስት ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሁሴን አል-ኢዚ በትዊተር ገጹ ገልጿል።
ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዩኬ በአሜሪካ እገዛ የመንን እና አጋሮቿን እያጠቃች ነው ብሏል።
የሀውቲ ታጣቂዎች በቀይ ባህር በሚንቀሳቀሱ መርከቦች ላይ ከባለፈው ህዳር ወር አጋማሽ ጀምሮ ጥቃት የሚያደርሱት ከእስራኤል ጋር እየተዋጋ ላለው የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ አጋርነት ለማሳየት መሆኑን ይገልጻሉ።
ሀውቲዎች በቀይ ባህር ላይ በሚያደርሱት ጥቃት በርካታ የንግድ መርከብ ኩባንያዎች አቅጣጫ ለመቀየር ተገድደዋል።
በቀይ ባህር የሚደረጉ የመርከብ እንቅስቃሴዎች ደህንነት ለማስጠበቅ፣ አሜሪካ እና ዩኬ በየመን ግዛት ውስጥ በሀውቲ ይዞታዎች ላይ ተደጋጋሚ ድብደባ አካሂደዋል።
ይሁን እንጅ የሀውቲ ታጣቂዎችም በመርከቦች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት አላቆሙም።