በባለፈው ሳምንት ውስጥ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያለው መርከብ አላለፈም- የሀውቲ ታጣቂዎች
ሀውቲዎች በሚያደርጉት ጥቃት ምክንያት በርካታ የመርከብ ድርጅቶች የቀይ ባህር መስመርን ለመቀየር ተገድደዋል
የሀውቲ ታጣቂዎች ከባለፈው ህዳር ወር አጋማሽ ጀምሮ በአለምአቀፍ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት እየሰነዘሩ ናቸው
በባለፈው ሳምንት ውስጥ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያለው መርከብ እንዳያልፍ ማድረጋቸውን የሀውቲ ታጣቂዎች አስታወቁ።
በኢራን የሚደገፉት የሀውቲ ታጣቂዎች መሪ በትናንትናው እለት እንዳስታወቁት ባለፈው ሳምንት ውስጥ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸው መርከቦች በኤደን ባህረ ሰላጤ እንዳያልፉ አድርገዋል።
"አሜሪካ እና እንግሊዝ መርከብ ለማሳለፍ ያደረጉት ጥረት ሳይሳካላቸው ቀርቷል። መርከቦቻቸውን መከላከል አልቻሉም። ከዚህ በኋላም መከላከል አይችሉም፤ ይህ ለእኛ ትልቅ ድል ነው" ሲል አብዱል ማሊክ አል ሀውቲ በቴሌቪዥን በተላለፈ መልእክት ተናግሯል።
አብዛኛውን የየመን ክፍል የተቆጣጠሩት የሀውቲ ታጣቂዎች ከባለፈው ህዳር ወር አጋማሽ ጀምሮ በአለምአቀፍ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት እየሰነዘሩ ናቸው።
የመርከብ እና የኢንሹራንስ ድርጅቶች እንደሚሉት ከሆነ ታጣቂዎቹ ከአሜሪካ፣ ከእንግሊዝ እና እስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸውን መርከቦች ኢላማ ያደርጋሉ።
ታጣቂዎች በመርከቦቹ ላይ ጥቃት የሚሰነዘሩት ከእስራኤል ጋር እየተዋጋ ላለው ለፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ አጋርነት ለማሰየት መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።
መሪው አብዱል ማሊክ አል ሀውቲ እንደገለጸው በጋዛ በከበባ ውስጥ ያሉ ዜጎችን ለመታደግ የሚደረገው ጥቃት ህጋዊ ነው ብሏል።
ሀውቲዎች በሚያደርጉት ጥቃት ምክንያት በርካታ የመርከብ ድርጅቶች የቀይ ባህር መስመርን ለመቀየር ተገድደዋል።
አሜሪካ እና አጋሮቿ በቀይ ባህር ላይ ያለውን የመርከቦች እንቅስቃሴ ለማስጠበቅ የመን ውስጥ የሀውቲ ይዞታዎችን ደብድበዋል።
ነገርግን ታጣቂዎቹ በቀይ ባህር በሚንቀሳቀሱ መርከቦች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ቀጥለዋል።