በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉት የየመን ሀውቲ ታጣቂዎች በቀይ ባህር ላይ ሲጓዝ በነበረ እቃ ጫኝ መርከብ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን በዛሬው እለት ገልጸዋል
የየመን ሀውቲ ታጣቂዎች በቀይ ባህር ላይ ሲጓዝ በነበረ መርከብ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ገለጹ።
በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉት የየመን ሀውቲ ታጣቂዎች በቀይ ባህር ላይ ሲጓዝ በነበረ እቃ ጫኝ መርከብ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን በዛሬው እለት ገልጸዋል።
የቡድኑ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሬ በቴሌቪዥን በተላለፈ መልእክቱ ጥቃት የተሰነዘረባት መርከብ የአሜሪካ መሆኗን ቢገልጽም፣ የመርከቦችን የባህር ላይ እንቅስቃሴ የሚቆጣጠረው ጠቋሚ ግን የማርሻል ደሴት ሰንደቅአላማን ስታውለበልብ የነበረችው መርከብ ንብረትነቷ የግሪክ ነው ብሏል።
የእንግሊዝ የማሪታይም ሴኩሪቲ ፊርም የሆነው አምብሬይ እና የዩናይትድ ኪንግደም ማሪታይም ትሬድ ኦፐሬሽን (ዩኬኤምቲኦ) ታጣቂዎቹ ስለጥቃቱ ከመናገራቸው ቀደም ብለው እንደገለጹት የማርሻል ደሴት ሰንደቅ አላማ ስታውለበልብ የነበረች መርከብ በባብኤል ማንዴብ በኩል ስታልፍ ሁለት ጊዜ ሚሳይል ተተኩሶባታል።መርከቧ ተመታ ጉዳት እንደደረሰባት አምብሬይ ገልጿል።
አብዛኛውን የየመን ክፍል የተቆጣጠሩት የሀውቲ ታጣቂዎች ከህዳር አጋማሽ ጀምሮ በአለምአቀፍ የንግድ መርከቦች ላይ የድሮን እና የሚሳይል ጥቃት እያደረሱ ናቸው።
ሀውቲዎች ጥቃቱን የሚሰነዝሩት ከእስራኤል ጋር እየተዋጋ ላለው ለፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ አጋርነት ለማሳየት መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል። በጥቃቱ ምክንያት በርካታ የመርከብ ኩባንያዎች በቀይ ባህር የሚያደርጉትን ጉዞ በመተው ረጅሙን እና ወጭ የሚያስወጣውን መስመር ለመጠቀም እንዲገደዱ እያደረጋቸው ይገኛል።
በቀይ ባህር ላይ የሚደረገውን የመርከቦች እንቅስቃሴ ሰላማዊ ለማድረግ፣ አሜሪካ በየመን ውስጥ ዘልቃ በመግባት በሀውቲ ይዞታዎች ላይ ጥቃት ማድረስ ከጀመረች ሳምንታትን አስቆጥራለች።