ግዙፍ የመርከብ ኩባንያዎች የቀይ ባህርን መስመር ለመተው መገደዳቸው ተገለጸ
የሀውቲ ታጣቂዎች ጥቃት የሚሰነዝሩት ከእስራኤል ጋር እየተዋጋ ላለው ሀማስ አጋርነት ለማሳየት ነው
የሀውቲ ታጣቂዎች በቀይ ባህር ወደ እስራኤል በሚያቀኑ መርከቦች ላይ ጥቃት እንደሚያደርሱ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል
ግዙፍ መርከብ ኩባንያዎች የቀይ ባህርን መስመር ለመተው መገደዳቸው ተገለጸ።
የሀውቲ ታጣቂዎች የሚያደርሱት ጥቃት በመጨመሩ ምክንያት የመርከብ ኩባንያዎች ቀይ ባህርን ለመተው ተገደዋል።
የሀውቲ ታጣቂዎች ከእስራኤል ጋር እየተዋጋ ላለው ሀማስ አጋርነት ለማሳየት በቀይ ባህር በኩል በሚያልፉ መርከቦች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት አጠናክረው ቀጥለዋል።
በዚህ ጥቃት ምክንያት የተወሰኑ ግዙፍ የመርከቡ ኩባንያዎች መስመር መቀየራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
የቀይ ባህር መስመርን መጠቀም ለመተው ከወሰኑት ኩባንያዎች መካከል ዋናዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው።
-ሲኤምኤሲጂኤም(ሲኤምኤዩኤል)
የፈረንሳዩ የመርከብ ቡድን የሆነው ሲኤምኤሲጂኤም ታህሳስ 16 የቀይ ባህርን መስመር መጠቀም ማቆሙን አስታውቋል።
-ኤችኤልኤጂዲኢ
የጀርመን ኮንቴነር ሺፒንግ ኩባንያ የሆነው ኤችኤልኤጂዲኢ አንደኛው መርከቡ ከተጠቃበት ከሰአታት በኋላ ቀይ ባህርን መጠቀም ለማቆም እያሰበበት እንደሆነ ገልጿል።
ከድሮን እንደተተኮሰ የሚታመን መሳሪያ አል ጃስራህ የተባለችውን መርከብ መትቷል። በመርከቧ ስራተኞች ላይ የደረሰ ጉዳት የለም።
-ኤምኢአርኤስኬ
የዴንማርኩ የመርከብ ኩባንያ ኤፒ ሞለር መርስቅ አንድ ኮንቴነር የጫነች መርከብ ለትንሽ ማምለጧን ተከትሎ ሁሉም መርከቦች በቀይ ባህር በኩል እንዳይሄዱ ወስኗል።
ኩባንያው እንደገለጸው መርከቧ ከኦማን ወደ ሳኡዲ አረቢያ፣ ጂዳ እያመራች ባለችበት ወቅት ጥቃት ተሰንዝሮባታል።
-ኤምኤስሲ
የሜዲትራኒያን ሺፒንግ ኩባንያ(ኤምኤስሲ) ከሀውቲ ጥቃት ከአንድ ቀን በኋላ መርከቦቹ በሲውዝ ካናል በኩል እንደማይጓዙ እና የተወሰኑትም ወደ ኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ ማምራታቸውን ታህሳስ 16 አስታውቋል።
ውሳኔው የጉዞ መርሃ ግብሮችን ማዛባቱን ድርጅቱ ገልጿል።
-ኦኦሲኤል
ባለቤትነቱ መቀመጫውን ሆንግ ኮንግ ያደረገው ኦሬንታል ኦቨርሲ የሆነው ኦሬንት ኦቨርሲ ኮንቴነር ላይን(ኦኦሲኤል) ወደ እስራኤል የሚገቡ እና የሚወጡ እቃዎችን መቀበል ማቆሙን ታህሳስ 16 አስታውቋል።
የሀውቲ ታጣቂዎች በቀይ ባህር በኩል ወደ እስራኤል በሚያቀኑ መርከቦች ላይ ጥቃት እንደሚያደርሱ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።