አሜሪካውያን ከምርጫ ውጥረት ራሳቸውን ገለል ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረጉ ነው
ከነገው ምርጫ በኋላ ምን ሊከሰት ይችላል በሚል በርካታ ዜጎች ጭንቀት ውስጥ ይገኛሉ ተብሏል
ምርጫው የአሜሪካ የዴሞክራሲ ጉዞን የሚወስን ሊሆን እንደሚችል ከ50 በመቶ በላይ መራጮች እምነት አላቸው
አሜሪካውያን ዜጎች ከምርጫ ውጥረት ራሳቸውን ለማግለል የተለያዩ ጥረቶችን እያደረጉ እንደሆነ ተስምቷል፡፡
ከምርጫው ጋር በተያያዘ “ድምጽ የሰጠሁት ዕጩ ሊሸነፍ ይችላል” በሚሉ እና ከድህረ ምርጫ በኋላ ብጥብጥ ሊፈጠር እንደሚችል በመስጋት ዜጎች ውጥረት ውስጥ እንደሚገኙ ነው የተነገረው፡፡
መራጮች ከዚህ ጭንቀት ገሸሽ ለማለት እና ትኩረታቸውን ሌሎች ስፍራዎች ላይ ለማዋል የዜና ጣብያዎችን ያለመከታተል፣ ስልኮቻቸውን ማጥፋት፣ ሀይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ መሳተፍ ፣ መጽሀፍ ማንበብ፣ ዋና፣ ዮጋ እና ሌሎች ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በማዘወተር ላይ ይገኛሉ፡፡
በአንዳንድ ስፍራዎች ለመጪዎቹ በዓላት ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ ሲሆን ፤ ቀደም ብሎ የገና ዛፎችን ቤታቸው ውስጥ በማስቀመጥ እና የተለያዩ ማስዋቢያዎችን በመኖርያ ግቢያቸው አካባቢ በመስቀል የትኩረት አቅጣጫቸውን ለማሰቀየር እየጣሩ ነው፡፡
አሶሼትድ ፕረስ በቅርቡ ከመራጮች በሰበሰበው የህዝብ አስተያየት ከአስር አሜሪካውያን አራቱ ከዘንድሮው ምርጫ በኋላ ግጭት ሊፈጠር እንደሚችል እንደሚያምኑ አመላክቷል፡፡
የድህረ ምርጫ ብጥብጥ እና ውጤቱን ለመቀልበስ የሚደረጉ ሙከራዎች የአሜሪካ ፖለቲካ ስርአት ላይ ተጽዕኖውን ሊያሳድር እንደሚችልም ስጋት አላቸው።
የዘንድሮው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የአሜሪካ የዴሞክራሲ ጉዞን የሚወስን ሊሆን እንደሚችል ከ50 በመቶ በላይ መራጮች ያምናሉ፡፡
ቀደም ካሉት ምርጫዎች በተለየ ከፍተኛ ፉክክር እንደሚደረግበት በሚጠቀው ከነገው ምርጫ በኋላ “ምን ሊከሰት ይችላል?” የሚለው ጥያቄ በበርካታ መራጮች ላይ ጭንቀትን ያስከተለ ጉዳይ ነው፡፡
ሮይተርስ የምርጫውን አሸናፊ ይወስናሉ በሚባሉ 7 ግዛቶች ያነጋገራቸው 50 ሰዎች፤ የሚመርጡት እጩ ቢሸነፍ ሀገሪቱ ምን አይነት መልክ እንደሚኖራት ፣ ተሸናፊው ወገን ውጤቱን ለመቀበል ያለው ዝግጁነት እና የፖለቲካ ክፍፍሉ እየጠነከረ ይሄዳል በሚሉ ጉዳዮች ውጥረት ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ብዙ መራጮች በተለይም ትራምፕ ከተሸነፉ የክስ ማዕበል እና የፍርድ ቤት ችሎቶች፣ ሰላማዊ ሰልፎች ባስ ሲልም ሁከት እና ብጥብጥ ሊፈጠር እንደሚችል ስጋት አድሮባቸዋል።
ትራምፕ ዴሞክራቶች ምርጫውን ካላጭበረበሩ በስተቀር ማሸነፍ እንደማይችሉ በተደጋጋሚ በእርግጠኝት ሲናገሩ ተደምጠዋል፤ ካማላ ሀሪስ በበኩላቸው የሪፐብሊካኑ ዕጩ ያለጊዜው ማሸነፋቸውን የሚያውጁ ከሆነ “እጋፈጣቸዋለሁ” ሲሉ ዝተዋል፡፡
አንዳንድ መራጮች የዜና ጣብያዎችን ትተው ስፖርታዊ ዜናዎችን ብቻ ለመመልከት ጥረት ቢያደርጉም በየመሀሉ የሚመጡ የምርጫ ማስታወቂያዎች የፈለጉትን እረፍት እንዳያገኙ እክል እንደሆኑባቸው ገልጸዋል፡፡
ሌሎች ደግሞ ከቤት ውስጥ በመውጣት አካላዊ እንቅስቀሴ ለማድረግ እንዲሁም በመዝናኛ ስፍራዎች ለማሳለፍ በሚያደርጓቸው ሙከራዎች የሰዎች ሁሉ ወሬ ምርጫ ላይ ብቻ በማተኮሩ በቤታቸው መቀመጥን መርጠዋል፡፡