ትራምፕ ምርጫውን አሸንፈው የዩክሬኑን ጦርነት ለማስቆም የሚሞክሩ ከሆነ ሊገደሉ እንደሚችል የቀድሞው የሩሲያ ፕሬዝዳንት ተናገሩ
ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ በነገው ምርጫ የትኛውም ዕጩ ቢያሸንፍ ከሩሲያ ጋር በተገናኘ ምንም የሚፈጥረው ለውጥ የለም ብለዋል
ትራምፕ የሚያሸንፉ ከሆነ ግን በዩክሬን ጉዳይ የጆን ኤፍ ኬንዲ እጣ ሊገጥማቸው ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል
የሩሲያ የደህንነት ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበር እና የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዝዳንት ሆነው ከተመረጡ እና የዩክሬንን ግጭት ለማስቆም የሚሞክሩ ከሆነ ሊገደሉ እንደሚችሉ ተናገሩ።
ትራምፕ በዩክሬን ጉዳይ እያንጸባረቁት ያለው አቋም ከአሜሪካ ምዕራባውያን አጋሮች እና ከሀገሪቱ ዋና ዋና ፓርቲዎች ፍጹም የተለየ ነው ያሉት የቀድሞ ፕሬዝዳንት ይህ አቋማቸው ጥላት የሚያነሳሳባቸው ሊሆን እንደሚችል አሳስበዋል፡፡
ትራምፕ የጆን ኤፍ ኬኔዲ እጣ ፈንታ ሊገጥማቸው እንደሚችል ያስጠነቀቁት ሜድቬዴቭ፤ በአቋማቸው ጸንተው ጦርነቱን ለማስቆም ቢገፉ እንኳን የፓርቲ እና የፖለቲከኞች ተጽዕኖ እንዳሰቡት እንዳይራመዱ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ነው የተናገሩት፡፡
በዚህም በአንድ ቀን አይደለም በሶስት ቀን እና በሶስት ወራት የዩክሬንን ጦርነት ማስቆም ይችላሉ ብየ አላምንም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የሪፐብሊካ እጩ በምርጫው ካሸነፉ በዩክሬን ያለውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በ24 ሰአታት ውስጥ እንደሚያስቆሙ በተደጋጋሚ ቃል ገብተዋል፤ ሆኖም ጦርነቱን ስለሚያስቆሙበት መንገድ ዝርዝር ሁኔታዎችን አልገለጹም፡፡
ተቀናቃኛቸው ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ በበኩላቸው ትራምፕ የሚያሸንፉ ከሆነ ዩክሬን እጇን እንድትሰጥ ሊያስገድዱ ይችላሉ ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
የቀድሞው የሩስያ ፕሬዝዳንት ሜድቬዴቭ በማክሰኞው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የትኛውም እጩ ቢያሸንፍ በዋሽንግተን እና በሞስኮ መካከል ያለው ግንኙነት የሻከረ ሆኖ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡
ከሩሲያ ቱደይ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት “ለሩስያ የሁለቱም እጩዎች ማሸነፍ የሚቀይረው ነገር የለም ምክንያቱም ትራምፕም ሆኑ ከማላ የሩሲያን መሸነፍ አጥብቀው የሚመኝ ተመሳሳይ አቋም ስለሚያንጸባርቁ ነው” ብለዋል፡፡
ሃሪስን በተመለከተ “በኦባማ ቤተሰቦች እና በቀድሞ የአሜሪካ ባለስልጣናት የሚጎተቱ ልምድ አልባ እጩ” ሲሉ ጠርተዋቸዋል፡፡
በተጨማሪም “ምዕራባውያን ሀገሮች በተለይም አሜሪካ ከሩሲያ ጋር የደህንነት ስምምነት ለማድረግ በቂ ተለዋዋጭነት እና ጥበብ ቢኖራቸው ኖሮ በዩክሬን ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ አይደረግም ነበር” ብለዋል ።
ሜድቬዴቭ ትራምፕ ከየትኛው አካል ግድያ እንደሚቃጣባቸው በግልጽ ያሉት ነገር ባይኖርም በዩክሬን ጉዳይ የያዙት አቋም ትልቅ አደጋ ሊያስከትልባቸው አንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡