ከ160 ሚሊዮን በላይ አሜሪካዊያን ድምጽ እንደሚሰጡ ይጠበቃል
ነገ ስለሚጀመረው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እስካሁን የምናውቀው
የዓለማችን ልዕለ ሀያል ሀገር የሆነችው አሜሪካ 47ኛውን ፕሬዝዳንት ለመምረጥ ነገ ድምጽ በይፋ መስጠት ይጀመራል፡፡
ሀገሪቱ ከምርጫ ድምጽ መስጫ ቀን ቀደም ብሎ መምረጥ ለፈለጉ ሰዎች እንዲመርጡ የሚፈቅድ አሰራርን የምትፈቅድ ሲሆን እስካሁን ከ41 ሚሊዮን በላይ መራጮች ድምጽ ሰጥተዋል፡፡
በዚህ ምርጫ ላይ በምክትል ፕሬዝዳንትነት እያገለገሉ ያሉት ካማላ ሀሪስ ዲሞክራት ፓርቲን እንዲሁም ከአራት ዓመት በፊት በተካሄደ ተመሳሳይ ምርጫ በጆ ባይደን የተሸነፉት ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ ሪፐብሊካን ፓርቲን ወክለው ይወዳደራሉ፡፡
ምርጫው በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ዛሬ ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ሌሊት ላይ በይፋ የሚጀመር ሲሆን ከትንሽ ሰዓታት በኋላ አሸናፊው እጩ ይታወቃል፡፡
እጩዎቹ ካማላ ሀሪስ እና ዶናልድ ትራምፕ በተለይም የምርጫውን ውጤት የመቀየር አቅም አላቸው የሚባሉ ግዛቶች ላይ እየተዟዟሩ ቅስቀሳቸውን እያካሄዱ ናቸው፡፡
እስካሁን በተካሄዱ የቅድመ ምርጫ ጥናቶች ሁለቱም እጩዎች ምርጫውን የመሸነፍ እድል እንዳላቸው ተገልጿል፡፡
ታዋቂ ሰዎች እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ማንን እንደሚደግፉ አስቀድመው እያሳወቁ መምጣታቸው ምርጫውን የበለጠ አጓጊ እና የዓለምን ትኩረት እንዲስብ እያደረጉት ይገኛሉ፡፡
የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ ኢለን መስክ የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊ መሆኑን አስቀድሞ ሲያሳውቅ ጀኒፈር ሎፔዝ፣ ሌዲ ጋጋ፣ ቴይለር ስዊፍት እና ሌሎችም የካማላ ሀሪስ ደጋፊ ነን ሲሉ አሳውቀዋል፡፡
በነገው ምርጫ ላይ በአብላጫ ድምጽ የሚረጠው እጩ ጥር ወር ላይ ስልጣን በይፋ በመረከብ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት በመግባት ሀገሪቱን እና ዓለምን መምራት ይጀምራል፡፡