የ2024ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዕጩዎች ቁልፍ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አቋማቸው ምን ይመስላል?
የአለም ጂኦፖለቲክስን የሚወስነው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሊካሄድ ከአራት ቀናት ያነሰ ጊዜ ቀርቶታል
ተፎካካሪዎቹ በውጭ ጉዳይ ፖሊስ እና ሌሎች ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ያላቸው አቋም ከፍተኛ ልዩነት የሚንጸባረቅበት ነው
የ2024ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዕጩዎች ቁልፍ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አቋማቸው ምን ይመስላል?
የዴሞክራቷ እጩ ካማላ ሃሪስ እና ሪፐብሊካኑ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመጪው ማክሰኞ በሚደረገው ምርጫ አሸንፎ አሜሪካን ለመምራት ተፋጥዋል፡፡
በድራማ የተሞላው የዘንድሮ የአሜሪካ ምርጫ ከጆ ባይደን ዕጩነት መነሳት እስከ ትራምፕ የሁለት ጊዜ የግድያ ሙከራዎች በተለያዩ አዳዲስ አጋጣሚዎች ታጅቦ ወደ ወሳኙ ቀን ተቃርቧል፡፡
ተፎካካሪዎቹ በሰባት የፍልሚያ ግዛቶች በጠባብ የድምጽ ልዩነት አሸነፈው አሜሪካን ለመምራት ባለፉት ወራት የተለያዩ የምርጡኝ ቅስቀሳዎችን ሲያደርጉ ሰንብተዋል፡፡
በአሜሪካውያን ዜጎች ህይወት እና በአለም አቀፍ እጣ ፈንታ ላይ ወሳኝ ናቸው በተባሉ ከፅንስ ማቋረጥ መብት እስከ ህገወጥ ስደተኞች፣ ንግድ፣ ኢኮኖሚ ፣ የኑሮ ውድነት ፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፣ በአለም አቀፍ ደረጃ በተከሰቱ ጦርነቶች እና በሌሎች ቁልፍ አጀንዳዎች ላይ ለየቅል የሆነ ሀሳብን ያራምዳሉ፡፡
እጩዎቹ በወሳኝ ቁልፍ አጀንዳዎች ላይ ያላቸውን አቋም ጥቂቶቹን እንመልከት፡
የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ
በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ውስጥ ዩክሬን ፣ እስራኤል፣ የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ድርጅት ኔቶ እና በቻይና ዙርያ የሚከተሏቸው ፖሊሲዎች በዋናነነት ይጠቀሳሉ፡፡
ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረችበት ጊዜ አንስቶ የጆ ባይደን አስተዳደር ላለፉት አመታት ከ64.1 ቢሊየን ዶላር በላይ ወታደራዊ ድጋፍ አድርጓል፡፡
ከዚህ ባለፈም አስተዳደሩ ኔቶን ጨምሮ ሌሎች ምዕራባውያን ሀገራት እና ድርጅቶች ለኪቭ ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ በማስተባበር ግንባር ቀደሙን ሚና ተጫወቷል፡፡
ባለፉት ከሁለት አመታት ለዘለቁ ጊዜያትም በሩሲያ ወደ ውጭ በሚላኩ ምርቶች እና ባለስልጣኖች ላይ ማዕቀቦችን በማደረጃት እና በማስተግበር ሃሪስ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው፡፡ ከዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልደሚር ዘለንስኪም ጋር ለ7 ጊዜ ተገናኝተዋል፡፡
ጦርነቱ እንዲያበቃ ዩክሬን የተወሰኑ ግዛቶቿን ለሞስኮ አሳልፋ እንድትሰጥ የሚሰነዘሩ ሀሳቦችን “እጅ የመስጠት ሀሳቦች” ብለው የሚጠሩት ካማላ ሃሪስ በምርጫው የሚያሸንፉ ከሆነ የአሜሪካን ድጋፍ እንደሚያስቀጥሉ ቃል ገብተዋል፡፡
የዩክሬን ጦርነት ከመጀመሪያውም መነሳት ያልነበረበት ነው የሚል ጠንካራ እምነት ያላቸው ትራምፕ በበኩላቸው ለጦርነቱ መቀስቀስ እና መቀጠል የዩክሬኑን ፕሬዝዳንት እና የባይደንን አስተዳደር ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡
እርሳቸው ስልጣን የሚይዙ ከሆነ ግጭቱን በ24 ሰአታት እንደሚያስቆሙ ሲናገሩ በተደጋጋሚ የተደመጡት የቀድሞው ፕሬዝዳንት፤ ለዩክሬን በገፍ የጦር መሳሪያ ከማስታጠቅ ይልቅ ሰላማዊ አማራጮችን ማፈላለግ ዘላቂ መፍትሄ እንደሚሆን አምነት አላቸው፡፡
ቅድሚያ ለአሜሪካ በሚለው መርሀቸው የሚታወቁት ትራምፕ ለዩክሬን ጦር መሳርያ ድጋፍ የዋለውን በቢሊየን የሚቆጠር ድጋፍ “ኪሳራ” ሲሉ ጠርተውታል፡፡
ኪቭ ሞስኮን በጦርነት ማሸነፍ አትችልም ሲሉ በግልጽ የተናገሩት የሪፐብሊካኑ እጩ ዘለንስኪ የተወሰኑ ግዛቶችን ለሩሲያ በመልቀቅ ጦርነቱን ለመቋጨት መዘጋጀት እንዳለባት ይገልጻሉ፡፡
በእስራኤል ጉዳይ ሁለቱም ዕጩዎች ድጋፋቸው እንደማይናወጥ አቋማቸውን ይፋ ቢያደርጉም ሃሪስ ከትራምፕ በተለየ በፍልስጤማውያን ንጹሀን ላይ እየደረሰ በሚገኘው ጉዳት በጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ ላይ የሰላ ትችት በመሰንዘር ይታወቃሉ፡፡ ነገር ግን በድጋፍ ደረጃ ከጆ ባይደን የተለየ የፖሊሲ ለውጥ አንደማያደርጉ ይነገራል፡፡
በስልጣን ላይ እያሉ ጀምሮ እስካሁን የእስራኤል ጠንካራ ደጋፊ ሆነው የዘለቁት ትራምፕ የአሜሪካን ኤምባሲ ወደ እየሩሳሌም በማዛወር፣ በአረብ ሀገራት እና በእስራኤል መካከል በተከታታይ በተደረገው የሰላም ስምምነት ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ።
ትራምፕ እስራኤል በጋዛ ከሃማስ ጋር የምታደርገውን ውጊያ ቢደግፉም ግጭቱ በፍጥነት ማብቃት አለበት ብለዋል።
ቻይናን በተመለከተ ሃሪስ በስልጣን ዘመናቸው የቻይናን ተጽዕኖ ለመመከት ከእስያ ሀገራት ጋር ግንኙነትን ለማጠናከር በነበረው ጥረት በጃፓን ፣ ፍሊፒንስ ፣ ቬትናም እና ሌሎችም ሀገራት በመዘዋወር ዲፕሎማሲያዊ ስራዎችን ሰርተዋል፡፡
በዋሽንግተን እና በቻይና መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻልም የፕሬዚዳንት ጆ ባይደንን አካሄድ ያስቀጥላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአንጻሩ ዶናልድ ትራምፕ ከቻይና ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ ምርቶች ላይ ታሪፍ ለመጨመር ቃል ገብተዋል ፤ ይህም አዲስ የንግድ ጦርነት ሊያስከትል እንደሚችል ተሰግቷል፡፡
የቻይና ኩባንያዎች በአሜሪካ ሪል እስቴት እና መሠረተ ልማት ፣ በሃይል እና የቴክኖሎጂ ዘርፎችን በባለቤትነት እንዳይዙ እንደሚከለክሉም ቃል ገብተዋል፡፡
ኢኮኖሚ እና ታክስ
ሃሪስ በዓመት ከ400 ሺህ ዶላር በላይ በሚያገኙ አሜሪካውያን ቤተሰቦች ላይ የግብር ተመኑን ማሳደግ ይፈልጋሉ፤ ነገር ግን ከዛ በታች ገቢ በሚያገኙ አሜሪካውያን ላይ ትራምፕ በ2017 ተግባራዊ ያደረጉትን እና በቀጣዩ አመት የሚጠናቀቀውን የታክስ ቅነሳ ማራዘም ይሻሉ፡፡
ከጉርሻ (ቲፕ) ላይ የሚወሰድ ታክስን ማስቀረት ፣ አዲስ ልጅ ለሚወልዱ ወላጆች 6 ሺህ ዶላር ለመስጠት እና ለአዲስ ቤት ገዢዎች 25 ሺህ ዶላር ብድር ለመስጠት ወጥነዋል፡፡
ትራምፕ በበኩላቸው በ2017 ተግባራዊ ያደረጉት የታክስ ቅነሳ ከኮቪድ በፊት የአሜሪካን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑን በመናገር መመሪያውን ለማስቀጠል ቃል ገብተውል፡፡
በተጨማሪም ከትርፍ ሰአት ስራ ክፍያዎች እና ከማህበራዊ ዋስትና ጥቅማጥቅሞች የሚቀነሰውን ታክስ አስቀራለሁ ብለዋል፡፡
ህገወጥ ስደተኝነት
ስደተኝነትን በተመለከተ ከዴሞክራቷ ካማላ በተለየ ጠንካራ አቋም ያላቸው የሪፐብሊካኑ እጩ በፕሬዝዳንትነታቸው ዘመን ያስጀመሩትን 725 ኪሎሜትር የሚረዝመውን የአሜሪካ ሜክሲኮ ድንበር ግንብ ማስጨረስ ይፈልጋሉ፡፡
በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ ወይም ሌሎች የኢሚግሬሽን ህጎችን ሲጥሱ የተያዙትን ስደተኞች በሙሉ እንደሚያስሩ እና ወደ ሀገራቸው እንደሚመልሱም ዝተዋል፡፡
በተጨማሪም የድንበር ደህንነተን ለማጠናከር ናሽናል ጋርድ እና አስፈላጊ ከሆም መደበኛ ወታደር እንደሚያሰማሩ፤ በአሜሪካ በህገወጥ መንገድ ገብተው ከሚኖሩ ስደተኞች የሚወለዱ ህጻናት የአሜሪካ ዜግነት እንዲያገኙ የሚፈቅደውንም ህግ ለመሰረዝ አቅደዋል፡፡
ዴሞካራቷ ሃሪስ ደግሞ ህጋዊ ስርአትን የተከተለ እና ሰብአዊነት በተላበሰ መንገድ ለታታሪ ሰዎች ዜግነት እንዲያገኙ እጥራለሁ ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የአሜሪካ ድንበር ወኪሎች፣ የኢሚግሬሽን ዳኞች እና የጥገኝነት ጠያቂዎች ሰራተኞችን ለማጠናከር ሴኔቱ ያቀረበውን የገንዘብ ድጋፍ ሀሳብ እንደሚደግፉም ይፋ አድርገዋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ ፣ ትምህርት ፣ ዴሞክራሲ ፣ ጽንስ ማቋረጥ እና ሌሎችም ቁልፍ ጉዳዮች ሁለቱ እጩዎች የተለያየ ሀሳቦች ከሚያንጸባርቁባቸው አጀንዳዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
በመጪው ማክሰኞ አሜሪካ 47ኛውን ፕሬዝዳንቷን ለመወሰን በመላ ሀገሪቱ ምርጫ ታካሂዳለች፡፡
አሸናፊው ከላይ በተጠቀሱት አጀንዳዎች እና በሌሎች ቁልፍ ጉዳዮች የሚከተለው ፖሊስ የአለምን እና የአሜሪካን ቅርጽ የሚወሰን ይሆናል፡፡