የሶሪያ አማጺያን የበሽር አል አሳድ አባት መቃብርን አቃጠሉ
በቃርዳሃ ከተማ የሚገኘው የሀፌዝ አል አሳድ መቃብር መቃጠል በተለይ የአሳድ አገዛዝ ደጋፊ የነበሩ አልዋይቲዎችን ስጋት ውስጥ ጥሏል
የሀያት ታህሪር አል ሻም መሪው አቡ መሀመድ አል ጆላኒ ግን ሶሪያ ከዚህ በኋላ የእምነት ነጻነት የሚከበርባት ሀገር ትሆናለች ሲል ቃል መግባቱ ይታወሳል
የሶሪያ አማጺያን የበሽር አል አሳድ አባት መቃብርን አቃጠሉ።
በወላጆቻቸው የትውልድ መንደር የሚገኘው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሀፌዝ አል አሳድ መቃብር መውደሙን የሚያሳዩ ምስሎች ወጥተዋል።
የሶሪያ ታጣቂዎች በሀያት ታህሪር አል ሻም መሪነት የአል አሳድ አገዛዝን ካስወገዱ በኋላ በመላው ሶሪያ የሚገኙ የቀድሞው ስርአት ምልክቶችን (ሃውልቶች) ሲያፈራርሱ ቆይተዋል።
በ13 አመቱ የእስር በርስ ጦርነት ብዙ ዋጋ የከፈሉ ሶሪያውያንም አደባባይ በመውጣት ከታጣቂዎቹ ጋር ደስታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል።
ስልጣን የጨበጡት ሃይሎች የአሳድ ቤተሰቦችን ሃውልቶች እንዳፈራረሱት በደጋፊዎቻቸው ላይ የበቀል እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ ወይ የሚለው የበርካቶች ስጋት ነው።
በሰሜን ምዕራብ ሶሪያ ቃርዳሃ በተሰኘች ከተማ የሚገኘው የሀፌዝ አል አሳድ መቃብር መቃጠልም በተለይ አልዋይቲዎችን እንዳሳሰበ ቢቢሲ ዘግቧል።
ከ1971 በአደጋ ህይወታቸው አልፎ ልጃቸው በሽር አል አሳድ ስልጣን እስከያዘበት 2000 ድረስ ሶሪያን ለ29 አመት የመሩት ሀፌዝ አል አሳድ ከአልዋይቲ ወላጆች ነው የተወለዱት።
አልዋይቲዎች ከሶሪያ ህዝብ 10 በመቶውን የሚሸፍኑና በላታኪያ ግዛት በብዛት የሚገኙ ሲሆን፥ የአሳድ አገዛዝ ዋነኛ ደጋፊዎች ነበሩ።
በመሆኑም የ53 አመታት የአሳድ አገዛዝን የጣሉት የታጠቁ ሃይሎች ኢላማ ያደርጉናል የሚል ስጋት አላቸው።
የተቃጠለው የሀፌዝ አል አሳድ መቃብር ከሚገኝባት ቃርዳሃ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎችን ድጋፍ ያገኙት የታጠቁ ቡድኖች ተወካዮች ግን በሃይማኖት እና ባህል ልዩነት ላይ የተመሰረተ ጥቃት ላለማድረስ መስማማታቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
ሶሪያ ከአሳድ አገዛዝ ነጻ ወጥታ ህዝቦቿም ተስፋን ቢሰንቁም የሃይማኖት ልዩነት እና የበርካታ ፖለቲከኞችና ታጣቂዎች ፍላጎት ሀገሪቱን መልሶ ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንዳይከታት ያሰጋል የሚሉ ተንታኞች አሉ።
በ2016 ከአልቃይዳ የተለየው የሀያት ታህሪር አል ሻም መሪው አቡ መሀመድ አል ጆላኒ ደማስቆን እንደተቆጣጠሩ የሶሪያን የሃይማኖት ብዙሃነት ለማክበርና ቃል መግባቱ ይታወሳል።
የሽግግር ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሀመድ አል ባሺርም "ሶሪያውያን አሁን የተገኘውን መረጋጋት የሚያጣጥሙበት ጊዜ ነው" ብለዋል።
የቢቢሲ ዘጋቢ በደማስቆ ሰዎች ወደ ስራ ገበታቸው እየገቡና ሱቆች እየተከፈቱ የመደበኛ ህይወት ጅማሮ እየታየ ነው ብሏል።