አወዛጋቢው ሰው አዲሱን ዘመቻ የከፈቱት በቀጣዩ ምርጫ የክርስቲያን ደጋፊዎቻቸውን ቁጥር ለማበራከት ነው ተብሏል
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መጽሃፍ ቅዱስ መሸጥ ጀመሩ።
ትራምፕ በራሳቸው ማህበራዊ ትስስር ገጽ (ትሩዝ ሶሻል) ደጋፊዎቻቸው “ፈጣሪ አሜሪካን ይባርክ” የሚል ስያሜ ያለውን መጽሃፍ ቅዱስ እንዲገዙ ጥሪ አቅርበዋል።
“ወደ ፋሲካ በዓል እየተቃረብን ነው፤ ‘ፈጣሪ አሜሪካን ይባርክ’ መጽሃፍ ቅዱስን በመግዛት አሜሪካ ዳግም እንድትጸልይ እናድርጋት” ሲሉም ነው መልዕክታቸውን ያስተላለፉት።
ሁሉም አሜሪካውያን በቤታቸው መጽሃፍ ቅዱስ ሊኖራቸው እንደሚገባም ነው ያነሱት።
ትራምፕ ዝርዝር ውስጥ መግባት ባልፈልግም መጽሃፍ ቅዱስ በህይወቴ ውስጥ ልዩ ቦታ አለው ብለዋል።
“ፈጣሪ አሜሪካን ይባርክ” መጽሃፍ ቅዱስ GodBlessTheUSABible.com በተሰኘ ድረገጽ በ59.9 ዶላር ለገበያ ቀርቧል ተብሏል።
ድረገጹ መጽሃፍ ቅዱስ በትራምፕ መተዋወቁ “ምንም አይነት ፖለቲካዊም ሆነ የምርጫ ቅስቀሳ” አላማ የለውም ማለቱንም አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት መጽሃፍ ቅዱሱን የሚያሳትመው ኩባንያ ባለቤት አለመሆናቸው ተገልጿል።
ይሁን እንጂ ዝናቸውን ተጠቅመው ለሰሩት የማስተዋወቅ ስራ ሊያገኙት ስለሚችሉት ገቢ የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድንም ሆነ መጽሃፍ ቅዱስ የሚሸጠው ኩባንያ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ዋይትሃውስ ዳግም ለመግባት ከባይደን ጋር የሚፎካከሩት ትራምፕ በቀረቡባቸው አራት ክሶች የገጠማቸውን የገንዘብ እጥረት ለመሙላት ባለፈው ወር በስማቸው የተሰየሙ ስኒከር ጫማዎችን ማስተዋወቃቸው ይታወሳል።
አዲሱ የመጽሃፍ ቅዱስ ግዙ ቅስቀሳም በወንጌላውያን አማኞች ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ትራምፕ በቀጣዩ ምርጫ ክርስቲያን ደጋፊዎቻቸውን ለማብዛት ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ተገልጿል።