የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ወደ አሜሪካ አቅንተዋል
የጆ ባይደን አስተዳደር እስካሁን ለዩክሬን ወደ 20 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ወታደራዊ እርዳታ አድርጓል
የዘሌንስኪ ጉብኝት የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከጀመረ ወዲህ የሚደረግ የመጀመሪያውና ታሪካዊ ጉብኝት መሆኑ ነው
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ወደ ዋሽንግተን አቅንተዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በአሜሪካ በሚኖራቸው ቆይታቸው ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና ከፍተኛ የብሄራዊ ደህንነት ረዳቶች ጋር እንደሚወያዩና በሀገሪቱ ኮንግረስን ንግግር እንደሚያሰሙም ተገልጿል፡፡
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ባህር ማዶ ተሻግረው የሚያደርጉት ጉብኝት የካቲት 24 ከተጀመረው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ወዲህ የሚደረግ የመጀመሪያውና ታሪካዊ ጉብኝት ነው ተብሎለታል፡፡
ጉብኝቱ ላላፉት 10 ወራት በበይነ መረብ ብቻ ሲያወሩ የነበሩት ሁለቱም መሪዎች በአካል ተገናኝተው በተለያዩ አንኳር ጉዳዮች ላይ የሚመክሩበትም ነው፡፡
ዘሌንስኪ ጉብኝቱን የዩክሬንን “የመቋቋም እና የመከላከል አቅምን” ለማጠናከር የአሜሪካ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑ ለዋይት ሃውስ ባለስልጣናት ለማስረዳት እንደሚጠቀሙበትም ሮይተርስ ምንጮቹን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡
ሚስጥራዊ እንደሆነ በተነገረለት ጉብኝት ወቅት ጆ-ባይደን ኪቭን ከሞስኮ ሚሳይሎች ጥቃት ለመከላከል የሚረዳ ፓትሪዮት ሚሳኤል ባትሪን ጨምሮ ወደ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ወታደራዊ ዕርዳታ ይፋ እንደሚያደርጉም አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለስልጣን ገልጸዋል።
የዋይት ሃውስ የፕሬስ ሴክሬታሪ ካሪን ዣን ፒየር በሰጡት መግለጫ “አሜሪካ ለዩክሬን ያላትን ዘላቂ ቁርጠኝነት ለማጉላት” ጆ-ባይደን ዘሌንስኪን ወደ ዋሽንግተን መጋበዛቸውን ተናግረዋል፡፡
ካሪን ዣን ፒየር "ጉብኝቱ ዩክሬን በኢኮኖሚ፣ ሰብአዊ እና ወታደራዊ ርዳታ አቅርቦትን ጨምሮ ዩክሬንን እስከሚፈቅደው ጊዜ ድረስ ለመደገፍ አሜሪካ ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት ያሳያል"ም ብለዋል፡፡
የጆ ባይደን አስተዳደር እስካሁን ለዩክሬን ወደ 20 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ወታደራዊ ርዳታ መስጠቱ መረጃዎች ያመልክታሉ፡፡
የዘሌንስኪ ጉዞ የተካሄደው ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረችበት ከ300 ቀናት በኋላ መሆኑ ነው፡፡
የሞስኮው ኃያል ሰው ፑቲን ዘመቻውን ሲጀምሩ ኪቭን በቀናተው ውስጥ በመያዝ አላማቸውን ለማስፈጸም የነበረ ቢሆንም፤ አሜሪካን ጨምሮ በምዕራባውያን ከፍተኛ ድጋፍ የሚደረግለት የዩክሬን ጦር እንዳሰቡት ቀላል እንዳልሆነላቸው ይነገራል፡፡
የዩክሬን ጦር በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየወሰደው ባለው የመልሶ ማጥቃት እርምጃና የሚቀዳጀው ድል ደግሞ በዩክሬን ምድር ያለው ቀውስ ሌላ መልክ እንዳይዝ የሚል በርካቶች በስጋት የሚያነሱት ጉዳይ ሆኗል፡፡