ሩሲያ ለዩክሬን ጦርነት ከ200 ሽህ በላይ አዲስ ወታደሮችን በማዘጋጀት ላይ ናት ተባለ
ሞስኮ ወደ ኪየቭ ተጨማሪ ጥቃት እንደምትሰነዝር የዩክሬን የጦር መሪ ተናግረዋል
የሞስኮ አዲስ ጥቃት በጥር ወር ሊከሰት ይችላል ተብሏል
የዩክሬን ፕሬዝዳንት እና ከፍተኛ የመከላከያ አዛዦች ሩሲያ በሚቀጥለው የፈረንጆቹ ዓመት መጀመሪያ ላይ አዲስ ጥቃት እንደምትጀምር ተንብየናል ብለዋል። ይህም የዩክሬንን ዋና ከተማ ኪየቭን ለመያዝ ሁለተኛ ሙከራን ያካትታል ተብሏል።
የመሪዎቹ ማስጠንቀቂያ የመጣው የምዕራባውያን አጋሮች ለዩክሬን ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ እና ወታደራዊ ስልጠና ሲሰጡ ነው።
የሞስኮ አዲስ ጥቃት በጥር ወር ሊከሰት ይችላል የተባለ ሲሆን፤ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ፣ ጀነራል ቫለሪ ዛሉዥኒ እና ጀነራል ኦሌክሳንደር ሲርስኪ ሐሙስ እለት ከዘ ኢኮኖሚስት መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ይህኑ ጠቅሰዋል ።
ባለስልጣናቱ ጥቃቱ ከምስራቃዊ ዶንባስ አካባቢ፣ ከደቡብ ወይም ከአጎራባች ቤላሩስ ሊጀመር እንደሚችል እና በኪዬቭ ላይ ሌላ የመሬት ጥቃትን ሊጨምር ይችላል ብለዋል። ይህም ሞስኮ በጦርነቱ መጀመሪያ ላይ ለመያዝ ያልቻለችው ነው ብለዋል።
"ሩሲያውያን ወደ 200 ሽህ የሚጠጉ አዳዲስ ወታደሮችን እያዘጋጁ ነው። ወደ ኪየቭ ሌላ ጥቃት እንደሚያደርጉ አልጠራጠርም" ሲሉ ጀነራል ዛሉዝኒ ተናግሯል።
የዩክሬን መከላከያ ሚንስትር ኦሌክሲይ ሬዝኒኮቭ ዘ ጋርዲያን ላይ ባሳተሙት ጽሁፍ ሩሲያ ሰፊ አዲስ ጥቃት ለማድረስ ማቀዷን የሚያሳዩ መረጃዎች እየጨመሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በጥቅምት ወር ሩሲያ ጦርነቱን ለመደገፍ ከመለመለቻቸው 300 ሽህ ወታደሮች መካከል ግማሹ ስልጠናውን ሲያጠናቅቁ አዲሱ እርምጃ በየካቲት ወር ሊከሰት እንደሚችል ሚንስትሩ ገምተዋል።
ዩሮ ኒውስ እንደዘገበው ሁለቱም ወገኖች በፈረንጆች ገና እርቅ እንደማይፈልጉ ገልጸዋል።
በአሁኑ ጊዜ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በአውሮፓ ትልቁ የሆነውን ግጭት ለማስቆም ያለመ ድርድር የለም ተብሏል።