ልጆች የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን እንዲጠቀሙ ማድረግ ጉዳቱ ምን ያህል ነው?
ልጆች በቀን ውስጥ ለምን ያህል ጊዜ ኤሌክትሮኒክስ እንዲጠቀሙ ይመከራል?
ስልክ እና ቴሌቪዥኖችን አብዝተው የሚጠቀሙ ልጆችን እንዴት ማስቆም ይቻላል?
ልጆች ኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን እንዲጠቀሙ ማድረግ ጉዳቱ ምን ያህል ነው?
ያለንበት ዘመን የቴክኖሎጂ ዘመን መሆኑን ተከትሎ ዙሪያችን ሁሉ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ያሉበት ነው፡፡
ይህን ተከትም ወላጆች አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ለልጆች የእጅ ስልኮችን፣ ቴሌቪዥኖችን፣ ጌሞችን እና ማህበራዊ ሚዲያዎችን እንዲመለከቱ ያደርጋሉ፡፡
ተመራማሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ህጻናት አብዝተው ለኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ከተጋለጡ ከስነ ልቦና እና አዕምሮ ህመሞች ጋር የመጋለጥ እድላቸው ይጨምራል፡፡
ይሁንና ልጆች ለምን ያህል ጊዜ ነው ኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን መጠቀም ያለባቸው? ቢጠቀሙስ በትክክል ሊደርስባቸው የሚችለው ችግሮች ምን ምን ናቸው? ባለማወቅ ልጆቻቸውን ለብዙ ጊዜ ኤሌክትሮኒክስ እንዲጠቀሙ ያደረጉ ወላጆች እንዴት ማስቆም ይችላሉ? የሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ ይሻሉ፡፡
ዩሮ ኒውስ በጉዳዩ ዙሪያ ባለሙያዎችን እና ጥናቶችን ዋቢ አድርጎ ሰፊ ዘገባ ሰርቶበታል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ ልጆች አብዝተው የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን የሚጠቀሙ ከሆነ የባህሪ እና የስሜት ችግሮች ይደርስባቸዋል፡፡
ቴክኖሎጂዎች ነገሮችን ቀላል ስለሚያደርጉ እና ልጆች አብዝተው እነዚህን ሲጠቀሙ በእውን ዓለም ችግሮች ሲያጋጥሟቸው ብስጩ እና ቁጡ መሆን፣ ራስን ማሳነስ እና ከሰዎች ጋር የመግባባት ችሎታ እንዲያንሳቸው ያደርጋሉ ተብሏል፡፡
የአዕምሮ እድገት ከልጅነታቸው ጀምሮ ሂደቱን ተከትሎ ካላደገ ለእድሜ ዘመን የማይፈቱ እና ውስብስብ ችግሮች ሊዳጋቸውም እንደሚችል በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ልጆች አብዝተው በኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ላይ ሲያዘወትሩ ቋንቋ አለማወቅ ወይም አፍ አለመፍታት፣ ከሌሎች ልጆች ጋር አለመግባባት እና ተያያዥ ለሆኑ የአዕምሮ ውስንነቶች የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ እንደሚሆን በአውስትራሊያው ሰንሻየን ዩንቨርሲቲ የህጻናት እና አዋቂ አዕምሮ እድገት ፕሮፌሰር ዶክተር ሚካኤል ናጀል ተናግረዋል፡፡
ለረጅም ጊዜ ቴሌቪዥን መመልከት የሚያስከትለው የጤና ተጽዕኖ ምንድን ነው?
እንዲሁም ስሜትን አለመቆጣጠር፣ኦቲዝም እና ራስን ማግለል ለተሰኙ ችግሮችም እንደሚጋለጡ ፕሮፌሰሩ ገልጸዋል፡፡
ኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን ሙሉ ለሙሉ ለልጆች ማራቅ የራሱ ጉዳት ቢኖረውም እስከ ሁለት ዓመት ድረስ ያሉ ህጻናት ምንም አይነት ኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን እንዳይጠቀሙ ባለሙያው መክረዋል፡፡
እንዲሁም ከ2 እስከ አምስት ዓመት ለሆኑ ህጻናት የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን የሚጠቀሙበት ጊዜ በቀን ውስጥ ከአንድ ሰዓት መብለጥ የለበትምም ተብሏል፡፡
ከ5 ዓመት እስከ 17 ዓመት ውስጥ ያሉ ልጆች ደግሞ በቀን ውስጥ በስክሪኖች ላይ የሚያሳልፉት ጊዜ ከ2 ሰዓት መብለጥ እንደሌለበት ባለሙው አሳስበዋል፡፡
በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ልጆቻቸው አብዝተው የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን የሚስጠቅሙ ወላጆች ልጆቻቸውን ከዚህ ለማላቀቅ ልዩ ትኩረት መስጠት አለባቸው የተባለ ሲሆን በተለይም የሰዎችን አይን ደፍረው እያዩ እንዲያወሩ ማለማመድ፣ ከእኩዮቻቸው ጋር እንዲጫወቱ ማድረግ፣ ቀስ በቀስ የልጆቹን የስክሪን ቆይታ መቀነስ፣ ስሜታቸውን እንዲቆጣጠሩ ማለማመድ፣ እንዲያወሩ ማበረታታት፣ እና ሌሎችንም እድገቶች እንዲያሳዩ መስራት እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡