“የስደተኞችን የወንጀል ድረጊቶች ለመቅረፍ ከፖሊስና ኢምግሬሽን ጋር እየሰራን ነው” የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን
ዳይሬክተሩ ከስደተኞች ጋር በተያያዘ “ዓለም የተሸከምነውን ኃላፊነት ሊረዳን ይገባል” ብለዋል
በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ 1 ሚልዮን የሚጠጉ ስደተኞች ይገኛሉ
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከ 27 ሀገራት በተለይም ከሶማልያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ኤርትራ የሚመጡ ስደተኞችን ታስተናግዳለች፡፡
የኢፌድሪ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር /ARRA/ መረጃ እንደሚያመለክተው ፣ አሁን ላይ 324,000 የደቡብ ሱዳን ፣ 217,000 የሚገመቱ የኤርትራ ፣ 200,000 የሶማልያ ፣ 67,000 የሱዳን ፣ እንዲሁም 5,400 የኬንያ ስደተኞች በኢትዮጵያ ይገኛሉ፡፡
በአጠቃላይ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ 1 ሚልዮን የሚጠጉ ስደተኞችን በማስተናገድ፡ በአፍሪካ ከኡጋንዳና ሱዳን ቀጥላ ኢትዮጵያ በሦስተኛ ደረጃ ተቀምጣለች፡፡
የ1951ዱን የስደተኞች ኮንቬንሽንና የ1967ቱን ፕሮቶኮልም የፈረመችው ኢትዮጵያ ፣ ከተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን /UNHCR/ እና ሌሎች ባለድርሻ አካለት ጋር በመሆን ዓለም አቀፋዊ ኃላፊነቷን እየተወጣች ትገኛለች፡፡
ይሁንና ኢትዮጵያ ከምታስተናግዳቸው የተለያዩ ሀገራት ስደተኞች ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎች አልታጡም፡፡ በተለይም ስደተኞቹ ከመጠለያ ውጭ እንቅስቃሴ በማድረግ ይፈጽሟቸዋሉ የሚባሉ የወንጀል ድረጊቶች እና የስራ እድል መቀራመት በዋናነት እንደ ችግር የሚነሱ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ አል-ዐይን በጉዳዩ ላይ የኢፌዴሪ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር /ARRA/ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይን ጠይቋል፡፡
የስደተኞች በወንጀል ድርጊቶች ላይ መሳተፍ
በቅርቡ ስደተኞች ፣ በተለይም ኤርትራውያን ስደተኞች ፣ በጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየሞች) አካባቢ በሚፈጥሩት የድምጽ ብክለት “ነዋሪዎች ቤታቸውን አከራይተው ከአካባቢው እንዲርቁ” ምክንያት ከመሆን ባለፈ ፣ “ተደራጅተው የመዝረፍ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉም” ቅሬታ እንደቀረባበቸው የሚታወስ ነው፡፡
የኢፌዴሪ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ እንደሚሉት ፣ በ2011 በወጣው የስደተኞች አዋጅ መሰረት መስፈርቶችን ያሟሉ ስደተኞቸ ከካምፕ ወጥተው የመኖር መብት አላቸው፡፡ ከመጠልያ ውጭ (out of Camp) ፖሊሲ ስደተኞች ከካምፕ ሲወጡ የካምፕ አገልግሎት እንደማያገኙ ደንግጎ ወጥተው መኖር እንደሚችሉ የሚፈቅድ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ከስደተኞች ጋር ተያይዘው ለሚነሱ የወንጀል ድርጊቶች (በህገ-ወጥ መንገድ ፓስፖርትና መታወቅያ ማውጣት እንዲሁም ፀጥታ ማደፍረስ) በተመለከተም ምልሽ ሰጥተዋል፡፡
“የሚነሳው ጥያቄ የሚካድ አይደለም” ያሉት አቶ ተስፋሁን ነገር ግን አሁን በኢትዮጵያ ያሉትን ስደተኞች ጉዳይ በሁለት ከፍሎ ማየት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ በአንድ በኩል የስደተኛ ሂደቶችን ተከትለው የመጡ ስደተኞች ሲኖሩ በሌላ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ሰላም መውረዱን ተከትሎ በቱሪስት ቪዛ በቀጥታ አውሮፕላን የገቡ /ስደተኛ ያልሆኑ/ ስለመኖራቸው አንስተዋል፡፡ ከዚህም ጋር በተያያዘ “በተጭበረበረ መንገድ የመታወቅያ ወይንም ፓስፖርት ማውጣት ጉዳይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱ ባይካድም ሁሉም ድርጊቶች በስደተኞቹ ተፈፅመዋል ለማለት ግን አያስደፍርም” ብለዋል አቶ ተስፋሁን፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ማንም ይሁን ማን ግን “ችግሩን ለመቅረፍ ከአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስና ኢምግሬሽን ጋር በጋራ እየሰራን ነው” ም ብለዋል አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ፡፡
የስራ እድልን መቀራመት
የዓለም አቀፉ ህግ ለስደተኞች የስራ ፈጣራ እድል ሊመቻች ይገባል እንደሚል ያስረዱት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ተስፋሁን ፣ ለዚህም 70 በመቶ የአከባቢ ማህበረሰብን እንዲሁም 30 በመቶ ስደተኞችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ታቅደው እንደሚዘጋጁም ተናግረዋል፡፡
ስራ የመቀራመት ዝንባሌዎች እዚህም ሆነ እዚያም የሚስተዋሉ ችግሮች መሆናቸውን የገለፁት አቶ ተስፋሁን፣ “ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር እየተሰራ ነው፤ ምክንያቱም የስራ መቀራመት ካለ በህዝቦች መካከል ክፍተት እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናልና” ብለዋል፡፡
ባጠቃላይ ኢትዮጵያ ለአፍሪካም ሆነ ለዓለም አቀፍ ሰላም ከምታበረክተው አስተዋፅኦ ባለፈ ስደተኞችን በማስተናገድ የምትወጣው ኃላፊነት በብዙዎች ዘንድ ያስመሰገናትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አመኔታና ክብር እንድታገኝም ያስቻላት መሆኑን አቶ ተስፋሁን ተናግረዋል፡፡ ይሁንና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚንፀባረቁ “የተሳሳቱ ግንዛቤዎች ሊጠሩ እንዲሁም ዓለም የተሸከምነውን ኃላፊነት ሊረዳን ይገባል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የኤርትራ ስደተኞችን ጉዳይ በአብነት የጠቀሱት አቶ ተስፋሁን “ባለፈው ጠቅላይ ሚኒሰትሩ በ ፓርላማ እንደተናገሩት አሁን ዓለም የኤርትራ ስደተኞችን በተመለከተ የያዘው ምስል ተገቢ ያልሆነ ነው፡፡ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ ከማድረግ ይልቅ ለመፍጠር እየሞከረ ያለው ምስል ትክክል አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በጋምቤላ ብቻ 6100 ሄክራት ለስደተኞች የሰጠች ሀገር ናት ፤ ካምፖች ላይ ያለ ውሀ የተፈጥሮ ነው ፤ የህግ እና የደህንነት ከለላም የምትሰጥ ሀገር ናት፤ እናም ዓለም እየተባበራት አይደለም ፤ ይህ ትልቅ ጫና እየፈጠረባት ነው እናም ዓለም እውነታውን ሊረዳ ይገባል” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለስደተኞች የምታደርገው መስተንግዶ፡ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና የባህል ዲፕሎማሲ በማጠናከር ረገድም ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለውም ነው አቶ ተስፋሁነይ ለአል-ዐይን የገለፁት፡፡
ኢትዮጵያ ለስደተኞች ምግብና መጠልያ ከማዘጋጀት ባሻገር፡ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የትምህርት እድል በመስጠት ሁኔታዎች ሲመቻቹ ዜጎች ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ሀገራቸውና ህዝባቸው እንዲጠቅሙ እየሰራች ትገኛለች፡፡
አስካሁን ከውጭ ተቋማት ጋር በመተባበር ቁጥራቸው ከ200,000 የሚልቁ ስደተኞች ከአጸደ ህጻናት አስከ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ የትምህርት እድል ማግኘት ችለዋል፡፡ ከነዚህም 1,500 የሚሆኑት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመማር እድል ማግኘታቸውን ነው የኢፌድሪ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር /ARRA/ መረጃ የሚያስረዳው፡፡