ህንዳውያኑን ቱጃሮች የጫኑ 8 የግል ጄቶች እንግሊዝ እገዳውን ከመጣሏ ከደቂቃዎች በፊት ሎንደን ደርሰዋል
በርካታ ህንዳውያን ቱጃሮች በከፍተኛ የገንዘብ ወጪ የግል ጄቶችን ተከራይተው ወደ እንግሊዝ መግባታቸው ተነገረ፡፡
ቱጃሮቹ በአስር ሺዎች የሚቆጠር ፓውንድን ለጄት ኪራይ ከፍለው ወደ ሎንደን ያቀኑት እንግሊዝ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በእጅጉ እየተፈታተናት ባለችው ህንድ ላይ የጉዞ እገዳን ከመጣሏ በፊት ሃገራቸውን ለመልቀቅ በማሰብ ነው፡፡
በዚህም ጥቂት የማይባሉ ህንዳውያን ቱጃሮችን የጫኑ 8 የግል ጄቶች እንግሊዝ እገዳውን ከመጣሏ ከደቂቃዎች በፊት ሎንደን በሚገኘው ሉቶን ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ መድረሳቸው ተሰምቷል፡፡
እንግሊዝ ባሳለፍነው አርብ ነበር ከህንድ በሚመጡ ተጓዦች ላይ እገዳን የጣለችው፡፡
በእግዳው መሰረትም ከህንድ የሚመጡ እንግሊዛውን ለ10 ቀናት በተመረጡ ሆቴሎች ራሳቸውን አግልለው እንዲቆዩ ይገደዳሉ፡፡
ከ10 ቀናት በፊት ህንድ የነበሩ የሌሎች ሃገራት ዜጎች ደግሞ ወደ እንግሊዝ እንዳይገቡ ተከልክሏል፡፡
ይህን ክልከላ ለማምለጥም ነበር ህንዳውያኑ ቱጃሮች ገደቡ ተግባራዊ ከመደረጉ ከደቂቃዎች በፊት ወደ እንግሊዝ መግባትን የመረጡት፡፡
ባሳለፍነው አርብ ሉቶን ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ከደረሱት 8 የግል ጄቶች መካከል አራቱ ከሙምባይ፣ ሶስቱ ከዴልሂ አንዱ ደግሞ ከአህመድአባድ የተነሱ መሆናቸውንም ነው ታይምስ ኦፍ ኢንዲያ የዘገበው፡፡
ለአንድ ጉዞ እስከ 70 ሺ ፓውንድ ከፍለዋልም ነው ታይምስ ኦፍ ኢንዲያ ያለው፡፡
ህንድ በከፍተኛ የቫይረሱ ተጽዕኖ ውስጥ ትገኛለች፡፡ ከ4 ቀናት በፊት የነበረው ሪፖርት በ24 ሰዓታት ውስጥ 314,835 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን መጠቆሙ የሚታወስ ነው፡፡ ይህ ቀዳሚው ሪከርድ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ጠቅላላ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 17.3 ሚሊዬን መድረሱም ተነግሯል፡፡ ይህም ህንድን ከአሜሪካ ቀጥሎ በቫይረሱ የተጠቃች ሁለተኛዋ የዓለማችን ሃገር ያደርጋታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በሁኔታው በመስጋት ወደ ህንድ ሊያደርጉት የነበረውን ጉዞ መሰረዛቸው የሚታወስ ነው፡፡