ልዩልዩ
በህንድ በኮቪድ 19 ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ከ200 ሺህ ተሻገረ
በ24 ሰዓት 360 ሺህ 960 ሰዎች ኮቪድ 19 ሲገኝባቸው፤ የ3 ሺህ 293 ሰዎች ህይወት አልፏል
በህንድ እስካሁን በኮቪድ 19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 18 ሚሊየን ገደማ ደርሷል
በህንድ በኮቪድ 19 ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ከ200 ሺህ መሻገሩ ተነገረ።
በሀገሪቱ በ24 ሰዓት ውስጥ 3 ሺህ 293 ሰዎች በኮቪድ 19 ሳቢያ ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን፤ ይህንን ተከትሎም በሀገሪቱ በቫይረሱ ሳቢያ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 201 ሺህ 187 መድረሱን ሮይተርስ ዘግቧል።
በህንድ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት በመጨመር ላይ መሆኑን ተከትሎ የኦክሲጅን እጥረት፣ ህክምና አቅርቦት አቅም ማነስ እና የሆስፒታሎች መጨናነቅ ለሟቾች ቁጥር መበራከት ምክንያት መሆኑም ተነግሯል።
በሀገሪቱ በ24 ሰዓት ውስጥ 360 ሺህ 960 ሰዎች በኮቪድ 19 የተያዙ ሲሆን፤ ይህም በዓለም ላይ በአንድ ቀን የተመዘገበ ከፍተኛው የኮቪድ 19 ተጠቂዎች ቁጥር ነው ተብሏል።
ይህንን ተከትሎም በሀገሪቱ እስካሁን በኮቪድ 19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 18 ሚሊየን ገደማ መድረሱንም ነው መረጃዎች የሚያመላክቱት።
1 ነጥብ 35 ቢሊየን ህዝብ ባላት ህንድ ከኮቪድ 19 ጋር ተያይዞ የሀገሪቱ መንግስት እያወጣ ያለው የተጠቂዎች እና የሟቾች ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑን እና ከዚህም ሊበልጥ እንደሚችል ተመራማሪዎች ይናገራሉ።