በዩኤኢ ህገ-መንግስት አንቀጽ 53 መሰረት፤ ሉዓላዊ ም/ቤት ፕሬዝዳንት እና ም/ፕሬዝዳንትን የመምረጥ ስልጣን አለው
መጋቢት 11 ቀን 1961 አል ዐይን በተባለው የአቡ ዳቢ አካባቢ የተወለዱት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ዛሬ ቅዳሜ ግንቦት 6 ቀን 2014 ዓ/ም የዩኤኢ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል፡፡
ሼክ መሃመድ የወንድማቸውን የፕሬዝዳንት ሼክ ኸሊፋን ቢን ዛይድ አል ናህያንን ሞት ተከትሎ ነው በፕሬዝዳንትነት የተመረጡት፡፡
ለለውጥ ባላቸው ቀናዒ አስተሳሰብና ተራማጅነታቸው የሚጠቀሱት ሼክ መሃመድ እርሳቸው ጭምር አባል በሆኑበት በሃገሪቱ ከፍተኛ የኤሚሬት ገዢዎች ጠቅላይ ምክር ቤት ነው የተመረጡት፡፡
እንደፈረንጆቹ በ1971 በሼክ ዛይድ ቢን ሱልጣን አል ናህያን መሪነት የተመሰረተችው የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ህገ መንግስት፤ በ51ኛው አንቀጽ እንዳስቀመጠው ከሆነ "የፌዴሬሽኑ ሉዓላዊ ምክር ቤት ከአባላቱ መካከል የፌዴሬሽኑን ፕሬዝዳንት እና ምክትሉን ይመርጣል፤ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ፕሬዝዳንቱ በማይኖርበት ወቅት ተክቶ የሚሰራ ይሆናል" ሲል ይደነግጋል።
አንቀጽ 53 ደግሞ “ፕሬዚዳንቱ ወይም ምክትላቸው በሞት ወይም ከስልጣን የሚለቁበት ሁኔታ ከተፈጠረ ወይም የሁለቱም የስልጣን ዘመን (አምስት ዓመት) በሆነ ምክንያት ሲያበቃ የሀገሪቱ ሉዓላዊ ምክር ቤት የመሰየም ኃላፊነት አለበት” ይላል።
በዚህም የህገ መንግስቱ አንቀጽ 52፤ የተፈጠረውን የስልጣን ክፍተት ለሞሙላትና ተተኪውን ለመምረጥ ምክር ቤቱ ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ በአንድ ወር ውስጥ ስብሰባ የመጥራት ስልጣን እንዳለው ያመለክታል፡፡
የፕሬዚዳንቱ እና ምክትል ፕሬዝዳንቱ የስራ መደቦች ክፍት ከሆኑ ምን ይደረጋል?
በዩኤኢ አንቀጽ 53 እንደተቀመጠው ከሆነ “ሉዓላዊ ምክር ቤት፤ ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንት የስራ መደቦች በአንድ ላይ ክፍት ሲሆኑ፣ በሁለቱ ክፍት የስራ መደቦች ላይ አዲስ ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት ለመምረጥ፤ ምክር ቤቱ በህብረቱ አባላት ወይም በህብረቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ግብዣ ወዲያውኑ ይሰበሰባል”ይላል፡፡
በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ህገ መንግስት አንቀጽ 46 መሰረት የፌደራል ሉዓላዊው ምክር ቤት የሀገሪቱ የበላይ ባለስልጣን ነው።
ምክር ቤቱ የሰባቱን ኢሚሬቶች ማለትም የአቡ ዳቢ (ዋና ከተማው)፣ ዱባይ፣ ሻርጃህ፣ አጅማን፣ ኡም አል-ኩዋይን፣ ራስ አል-ካይማህ እና የፉጃይራህን ገዥዎች ያቀፈ ነው።
የፌዴራል ጠቅላይ ምክር ቤት
የፌደራል ጠቅላይ ምክር ቤት በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ውስጥ ከፍተኛው ህገ መንግስታዊ ስልጣን ያለው ሲሆን፤ የህዝብ ፖሊሲዎችን የሚያወጣ እና የፌዴራል ህጎችን የሚያጸድቅ ከፍተኛው የህግ አውጭ እና አስፈፃሚ አካል ነው።
የገዢዎች ሉዓላዊ ምክር ቤት የፌዴሬሽኑን አካል ከሆኑ ከሰባቱ ግዛቶች በተወከሉ አካላት የተዋቀረ ሲሆን ግዛቶቹ እያዳንዳቸው አንድ ድምጽ እንዳላቸው ይነገራል፡፡
የጠቅላይ ምክር ቤቱ ተግባራት
በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ህገ-መንግስት መሰረት፤ ምክር ቤቱ ለህብረቱ በተሰጡ ጉዳዮች ላይ አጠቃላይ ፖሊሲን በማውጣት የህብረቱን ዓላማና የኢሚሬትቶች የጋራ ጥቅሞችን የሚያረጋግጡ ነገሮች ይመለከታል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ምክር ቤቱ ዓመታዊ አጠቃላይ በጀትን ጨምሮ በህገ-መንግስት የተደነገጉ የተለያዩ የፌዴራል ህጎችን እና አዋጆች ያጸድቃል፡፡
ስምምነቶችን ማጽደቅ፣ የህብረቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ሹመት ማጽደቅ፣ የስራ መልቀቂያቸውን በመቀበል እና በህብረቱ ፕሬዝዳንት ሀሳብ መሰረት ከስልጣናቸው እንዲነሱ ማድረግ ከምክር ቤቱ ዋና ዋና ተግባራት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ሊዓላዊ ምክር ቤቱ ፤ የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት እና ዳኞች ሹመት ማጽደቅ፣በአጠቃላይ በፌዴሬሽኑ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር ማድረግ፣ የስራ ሂደት ስርዓቱን፣ በውሳኔዎቹ ላይ የድምፅ አሰጣጥ ዘዴን እና የምክር ቤቱን ውሳኔዎች ጨምሮ መተዳደሪያ ደንቦቹን ማዘጋጀት እንዲሁም የጠቅላይ ምክር ቤቱ ዋና ፀሃፊ የማቋቋምና ስራዎችን የመቆጣጠር ስልጣንም አለው፡፡
ሉዓላዊ ምክር ቤቱ የሚያሳልፈው ውሳኔ በአምስቱ አባላቶች አብላጫ ድምፅ የሚሰጥ ሲሆን፣ ይህ አብላጫ ቁጥር የአቡ ዳቢ ኤሚሬቶች እና የዱባይ ኤምሬትስ ድምጽን ያካተተ ከሆነ እና አናሳዎቹ በተጠቀሰው ለብዙሃኑን አስተያየት ተገዥ የሚሆኑ ይሆናል፡፡
የሉዓላዊ ምክር ቤት ስብሰባዎች አብዛኛውን ጊዜ በህብረቱ ዋና ከተማ እንደሚካሄዱ ቢታወቅም አሰፈለጊ ሆኖ ሲገኝ በቅድሚያ በተስማሙበት በማንኛውም ቦታ ሊሰበሰብ ይችላል።