የሼክ ኸሊፋ ቢን ዛይድ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ
የዩኤኢ መስራች የሼክ ዛይድ የበኩር ልጅ የሆኑት ኸሊፋ የአቡ ዳቢ 16ኛው ገዢ ነበሩ
ስርዓተ ቀብሩ ትናንት አርብ ነው በትውልድ ሃገራቸው አቡ ዳቢ የተፈጸመው
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች (ዩኤኢ) ፕሬዝዳንት ሼክ ኸሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ፡፡
ስርዓተ ቀብሩ ትናንት አርብ ነው በትውልድ ሃገራቸው አቡ ዳቢ የተፈጸመው፡፡
ከስርዓተ ቀብሩ በፊት የአቡ ዳቢው ልዑል አልጋወራሽ ወንድማቸው ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን እና ሌሎች የቤተሰብ አባላቶቻቸውና የቅርብ ዘመዶቻቸው በተገኙበት የጸሎትና ስንብት መርሐ ግብር ተከናውኗል፡፡
መርሐ ግብሩ በዩኤኢ የመጀመሪያ እንደሆነ በሚነገርለትና በአቡ ዳቢ በሚገኘው ሼክ ሱልጣን ቢን ዛይድ መስጊድ ነው የተካሄደው፡፡
ከዚያም ሼክ መሃመድ እና ሌሎች የሼክ ኸሊፋን አስከሬን አጅበው በክብር ከቅብር ስፍራው አሳርፈዋል፡፡
ሼክ መሃመድ ዛሬ ቅዳሜ በአል ሙሽሪፍ ቤተ መንግስት በዚህ ከባድ የሃዘን ወቅት ከጎናቸው በመሆን የመጽናኛ መልዕክቶችን እንደሚቀበሉም የሃገሪቱ ዜና አገልግሎት ዋም ዘግቧል፡፡
እ.ኤ.አ በ1948 የተወለዱትና ዩኤኢን ከ2004 ጀምሮ በፕሬዝዳንትነት የመሩት ሼክ ኸሊፋ ትናንት አርብ በ73 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው መገለጹ ይታወሳል፡፡
የዩኤኢ መስራች የሼክ ዛይድ የበኩር ልጅ የሆኑት ኸሊፋ የአቡ ዳቢ 16ኛው ገዢ ነበሩ፡፡