የረመዳን ጾም ረጅም ሰአት የሚጾምባቸው የአለም ሀገራት
በተለያዩ አካባቢዎች ባለው የሰዓት አቆጣጠር ልዩነት ምክንያት እስከ 16 ሰዓታት የሚጾሙ አማኞች ቁጥር በርካታ ነው

በጾሙ ወቅት ጸሀይ ወደ ማደሪያዋ እስክትገባ ድረስ አማኞች ከምግብ፣ መጠጥ እና ሌሎችም ስጋዊ ፍላጎቶች ተቆጥበው ይውላሉ
በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው የረመዳን ጾም በአለም አቀፍ ደረጃ ከተጀመረ አንደኛ ሳምንቱን አስቆጥሯል፡፡
ሙስሊሞች የረመዳን ወር ከ1400 ዓመታት በፊት የቁርዓን የመጀመሪያዎቹ ክፍሎች ለነብዩ ሙሐመድ የወረዱበት ወቅት እንደሆነ ያምናሉ።
ከ29 እስከ 30 ቀናት በሚቆየው የጾም ወቅት ሙስሊሞች ከ12 እስከ 16 ሰአታት ከንጋት እስከ ምሽት ድረስ ከመብላት፣ መጠጣት እና ሌሎችም ስጋዊ ፍላጎቶች ታቅበው ይቆያሉ፡፡
እንደ ቺሊ እና ኒውዚላንድ ባሉ ደቡባዊው የአለም ሀገራት የሚኖሩ ሙስሊሞች ለ13 ሰአታት ያህል ይጾማሉ፤ በሰሜናዊው ጫፍ አይስላንድ እና ግሪንላንድን የመሳሰሉ ሀገራት ደግሞ በረጅሙ ቀኖቻቸው ለ16 ሰአታት ወይም ከዚያ በላይ ይጾማሉ።
ኖርዌን የመሳሰሉ በሰሜናዊ የአለም ክፍል የሚኖሩ ህዝቦች በአንዳንድ ወቅቶች ላይ ፀሀይ ለሶስት ሰአታት ብቻ የምትቆይበት ጊዜን ስለሚያስተናግዱ የሳኡዲዋን መካ ከተማን የሰአት አቆጣጠር በመከተል ጾሙን ያከናውናሉ፡፡
በሰሜናዊው ንፍቀ ክበብ ለሚኖሩ ሙስሊሞች በዚህ አመት የፆም ሰአት እያጠረ እስከ ፈረንጆቹ 2031 ድረስ ይቀጥላል። ከምድር ወገብ በስተደቡብ ለሚኖሩ ጾመኛ ሙስሊሞች ደግሞ በተቃራኒው ይሆናል።
በዚህም መሰረት የግሪንላንዷ ኑክ እና የአይስላንዷ ሬይክጃቪክ የእስልምና አማኞች ከተለመደው ሰዓት በተለየ 16 ሰዓታትን በጾም ላይ ያሳልፋሉ፤ በዚህም በረመዳል ለረጅም ሰዓት በመጾም ቀዳሚ በመሆን ይጠቀሳሉ፡፡