የአለማችን ታዋቂ መሪዎች ለምን ያህል ሰዓት ይተኛሉ?
ከሲሶ በላይ ህዝቧ ከሰባት ስአት በታች የሚተኛባት አሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ከ4 እስከ 6 ስአት እንደሚተኙ ይነገራል
ስፖርት የሚያዘወትሩት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸው ከ6 እስከ 7 ስአት እንደሚተኙ ገልጸዋል
ሀገር መሪዎች እና ፖለቲከኞች በበርካታ አንገብጋቢ ጉዳዮች በመወጠር በቂ እንቅልፍ እንደማያገኙ ይነገራል፤ ጫናው ከእንቅልፍ የማያናጥባቸው መሪዎችም አሉ።
አንዳንድ የሀገራት መሪዎች ከስልጣናቸው ከተነሱ በኋላ ጭምር ከእንቅልፍ ማጣት ጋር ለተገናኙ ችግሮች መጋለጣቸውን ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ከ440 ሺ በላይ በሚሆኑ አሜሪካውያን ላይ ከአመታት በፊት የተደረገ ጥናት ከሀገሪቱ ህዝብ ሲሶው ከ7 ስአት በታች እንደሚተኛ አመላክቷል።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቀን በአማካይ የሚተኙት አራት ስአት ብቻ መሆኑን “ቲንክ ላይክ ከ ኤ ቢሊየነር” በተሰኘው መጽሃፋቸው ላይ ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንቱ ከነጩ ቤተመንግስት ከወጡ በኋላም ከ4 ስአት በላይ እንደማይተኙ በ2024ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ተናግረዋል።
በዋይትሃውስ ለ10 ስአት፤ ከቢሮ ውጭ ደግሞ ለሶስት ስአት የመስራት ልምድ እንዳላቸው የተናገሩት 44ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማም ከፈረንጆቹ 1993 እስከ 2001 ሀገሪቱን ከመሩት ቢል ክሊንተን በተመሳሳይ ከአምስት እስከ ስድስት ስአት እንደሚተኙ ይፋ ማድረጋቸው አይዘነጋም።
36ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሊየንደን ጆንስን ደግሞ ከሁለት እስከ አራት ስአት ብቻ በመተኛት ስራቸው ላይ ተጠምደው ማሳለፋቸውን ነው ራዲዮ ሳዋ የሚያወሳው።
እንደ ጆን ኦፍ ኬነዲ እና ጆርጅ ደብሊው ቡሽ ያሉ የቀድሞ መሪዎችም መድሃኒቶችን በመውሰድ ለመተኛት እስከመገደድ ደርሰው እንደነበር ይታወሳል።
የ81 አመቱ የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንም ወደ ቢሯቸው በማለዳ ገብተው አመሽተው እንደሚወጡ የተገለጸ ሲሆን፥ በተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ ለሰከንዶች የተኙ መስለው መታየታቸው የእንቅልፍ እጦታቸው ማሳያ ሊሆን እንደሚችል ሲኤንኤን ዘግቧል።
የቀድሞው የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ሲልቪዮ ቤርሎስሎኒ እንቅልፍ ከራቃቸው መሪዎች መካከል ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው። ቢሊየነሩ መሪ በቀን በአማካይ ለ2 ስአት ብቻ ይተኙ እንደነበር ተዘግቧል።
የጀርመን መራሂተ መንግስት የነበሩት አንጌላ ሜርክልም “እንቅልፌን በእረፍት ስአቴ (ከስልጣን ሲነሱ) ለመተኛት እየቆጠብኩት ነው” በሚለው ንግግራቸው ይታወቃሉ።
የቀድሞዋ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርጋሬት ታቸር በቀን ለአራት ስአት ብቻ እንደሚተኙ ተናግረው ነበር።
የታቸር የእንቅልፍ እጦት የተጋባባቸው ዊንሰተን ቸርቺልም ከአራት ስአት በላይ እንደማይተኙ መናገራቸውን የእንግሊዝ መገናኛ ብዙሃን ያወሳሉ።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴያቸው የ71 አመት አዛውንት የማያስመስላቸው የሩሲይው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸው፥ “እንደማንኛውም ሰው በቂ እንቅልፍ አገኛለሁ፤ በቀን በአማካይ ከስድስት እስከ 7 ስአት እተኛለሁ፤ ብዙ ጊዜ ለስድስት ስአታት እተኛለሁ” ማለታቸው ይታወሳል።
የሀገራት መሪዎች የእንቅልፍ እጦት በጥሞና ሊያሳልፏቸው በሚገቡ ውሳኔዎች ላይ የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያደርስ ይታመናል።