ለ60 አመታት እንቅልፍ በአይኔ አልዞረም የሚሉት የ80 አመት አዛውንት
ቬትናማዊው ታይ ንጎክ በ20 አመታቸው ከገጠማቸው ከባድ ህመም በኋላ ከእንቅልፍ ጋር መለያየታቸውን ይናገራሉ
የህክምና ባለሙያዎች ግን አዛውንቱ ምናልባት ስለማይሰማቸው እንጂ በቀን ውስጥ የተወሰኑ ስአታት መተኛታቸው አይቀርም ባይ ናቸው
የሰው ልጅ አይደለም ለአመታት ለጥቂት ቀናት የእንቅልፍ መዛባት ከገጠመው በጤናው ላይ ምን ይዞ እንደሚመጣ መገመት አይከብድም።
ከወደ ቬትናም የተሰማው ዜና ግን ለአመታት መነጋገሪያ ሆኖ ዘልቋል።
በዚህ አመት 80ኛ አመታቸውን የያዙት ታይ ንጎክ፥ ላለፉት ስድስት አስርት አመታት እንቅልፍ ይዞኝ አያውቅም ይላሉ።
ቤተሰቦቻቸው፣ ጓደኞቻቸው እና ጎረቤቶቻቸውም ጭምር ንጎክ ተኝተው አይተዋቸው እንደማያውቁ ነው የሚገልጹት።
አዛውንቱ በፈረንጆቹ 1962 (የ20 አመት ወጣት እያሉ) ከገጠማቸው ህመም ወዲህ ከእንቅልፍ ጋር ተሰነባብተዋል።
ንጎክ በዘመናዊውም ሆነ ባህላዊ ህክምና ያልሞከሩት ነገር የለም፤ ከዛሬ ነገ ይሻሻላል ብለው የጠበቁት ጉዳይም ቀናት ቀናትን እየወለዱ ሲሄዱ እየተላመዱት መምጣታቸውን ይናገራሉ።
“የእንቅልፍ ማጣት ችግሩ በጤናዬ ላይ ያስከተለው ተጽዕኖ ስለመኖሩ እንጃ፤ እኔ እስካሁን ምንም ችግር አልገጠመኝም፤ ጤነኛ ነኝ፤ እንደማንኛውም አርሶ አደር ስራዬን እከውናለው” ብለዋል የ80 አመቱ አዛውንት ታህን ኔይን ከተሰኘው የቬትናም ድረገጽ ጋር ባደረጉት ቆይታ።
ድሪው ቢንስኪ የተባለ ዩትዩበርም በቅርቡ በእኝህ አዛውንት ቤት ካሜራውን ደቅኖ የተባለውን ለማረጋገጥ ሞክሯል።
ከአሜሪካ አሪዞና ወደ ገጠራማዋ የንጎክ መንደር የተጓዘው ድሪው “ከአመታት በፊት ዜናውን እንደተመለከትኩ ሊሆን አይችልም ነበር ያልኩት፤ በወቅቱ የአዛውንቱ መኖሪያ አካባቢ ስላልተገለጸም በአካል ሄጄ ለማረጋገጥ አልቻልኩም፤ አሁን ግን ከንጎክ ጋር ሌሊቱን ሙሉ ቁጭ ብዬ አድሬ እውነትነቱን በካሜራዬ ይዣለሁ” ይላል።
አሜሪካ በቬትናም ባካሄደችው ጦርነት (ከ1955 እስከ 1975) ምክንያት በእጃቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ንጎክ ምናልባትም በጦርነቱ የተመለከቷቸው ዘግናኝ ነገሮች እንቅልፍ እንዲያጡ ምክንያት ሳይሆኑ እንዳልቀረም ነው ድሪው የሚገልጸው።
የህክምና ባለሙያዎች ግን አዛውንቱ ምናልባትም ተኝተው እንቅልፍ የመያዝ ስሜት አልተሰማቸው ይሆናል እንጂ ሳይተኙ ለ60 አመታት መዝለቅ አይችሉም ይላሉ።
በአውስትራሊያ የእንቅልፍ እና ተያያዥ ጉዳዮች ሀኪም የሆኑት ዶክተር ቪካስ ዋድህዋ፥ አንዳንድ የእንቅልፍ መዛባት ችግሮች እንቅልፍ የመያዝ እና የመንቃት ስሜትን ለመለየት ያስቸግራሉ ብለዋል።
በመሆኑም የ80 አመቱ አዛውንት በቀን ውስጥ ለምን ያህል ስአት ወይም ደቂቃ እንደሚያርፉ ለማረጋገጥ ባይቻልም ቢያንስ አጭር ሸለብታ ይይዛቸዋል ነው የሚሉት።
ታይ ንጎክ በርግጥም ላለፉት ስድስት አስርት አመታት ከእንቅልፍ ከተለያዩ በምድራችን ረጅሙን እድሜ የኖሩ አዛውንት ይሆናሉ።
ምንክያቱም የሰው ልጆች በእድሜ ዘመናቸው በአማካይ ሲሶውን በእንቅልፍ ስለሚያሳልፉት።