የሰውነት ውፍረት መጨመርና ሰውነታችን መጠን በላይ መሞቅ ከእንቅልፍ እጦት ምልክቶች መካከል ናቸው
ሥራን በአግባቡ ለመስራት፣ ማህበራዊ ኑሮን ለማመጣጠም እንዲሁም ጤናማ ሆኖ ለመቆየት ጥሩ እንቅልፍ ወሳኝ መሆኑ ይታወቃል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የዛሬዋ እለት “የዓለም የእንቅልፍ ቀን” ተብላ የተሰየመች ሲሆን፤ ዋና ዓላማውም ጤናማ እንቅልፍ ያለውን ጠቀሜታ ለማስተማርና ሰዎች የተሻለ እና ጤናማ እንቅልፍ እንዲተኙ ግንዛቤ ለመፍጠር በማለም ነው የሚከበረው።
የእንቅልፍ ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ የተከበረው በፈረንጆቹ በ2008 ሲሆን፤ ቀኑንም የዓለም የእንቅልፍ ማህበረሰብ የተባለ ዓለም አቀፍ ተቋም ነው ያዘጋጀው።
አል ዐይን አማርኛ የዓለም የእንቅልፍ ቀንን በማስመልከት በቂ እንቅልፍ አለመተኛታችንን የሚያመላክቱ ምልክቶችን ሊያጋራችሁ ወዷል።
በቂ እንቅልፍ መተኛት ለጤናችን ጠቀሜታ እንዳለው እንደሚታወቅ ሁሉ፤ አይናችንን ከድነን ለመተኛች መቸገር ወይም በአግባቡ አለመተኛት ደግሞ ከድካም በዘለለ የጤና እክሎች እንደሚያስከትል የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ቀጥለው የተዘረዘሩት ምልክቶችም በቂ እንልፍ አለመተኛታችንን ያመለክታ እና ልብ ልንላቸው ይገባል።
የማስታወስ ችሎታችን መቀነስ
በርካታ ሰዎች ድካም ሲጫጫናቸው ነገሮችን የመስታወስ አቅማቸው በዚያው ልክ እየቀነሰ የሚመጣ ሲሆን፤ ይህም በቂ እንቅልፍ ማጣት የአእምሯችንን ነገሮችን የመማር እና ነገሮችን የማስታወስ አቅም ስለሚቀንስ ነው።
የእንቅልፍ እጦት ያለባቸው ሰዎች ነገሮችን ከመርሳት በተጨማሪም አንዳንዴ ሀሰተኛ ትዝታዎች እንደሚመጡባቸው በፈረንጆቹ በ2016 በሲንጋፖር የተሰራ ጥናት አመላክቷል።
የሰውነት ክብደት (ውፍረት) መጨመር)
የእንቅልፍ እጦት ወይም በቂ እንቅልፍ አለመተኛት ውፍረት ለመቀነስ የምናደርገውን ጥረት መና እንደሚያስቀር ባለሙያዎች ይናገራሉ።
እንደ ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ጥናት የእንቅልፍ ቆይታ የሰውነታችንን የመብላት ፍላጎት (አፒታይት) የሚቆጣጠሩ ሆርሞኖችን ምርት ጋር ግንኙነት እንዳለው ያመላክታል።
እንደ ጥናቱ ከሆነ በቂ ያልሆነ እንቅልፍ የምግብ ፍላጎታችንን የሚጨምር እና የረሃብ ስሜት እንዲሰማን የሚያደርገው ሆርሞን በብዛት እንዲመረት ያደርጋል።
በተጨማሪም በቂ ያልሆነ እንቅልፍ ጭንቀትን ይጨምራል የተባለ ሲሆን፤ ይህም በሰውነታችን ውስጥ ያለ የኮርቲሶል መጠን ከፍ እንዲል እንደሚያደርግ ነው የተነገረው፤ ይህም ለሰውነታችን መወፈር አይነተኛ ሚና አለው ተብሏል።
ሰውነታችን ከመጠን በላይ መሞቅ
እንቅልፍ ለሰውነታችንን ሙቀት ለመቆጣጠር አይነተኛ ሚና እንዳለው ተመራማሪዎች ይናገራሉ። ያለ እንቅልፍ ሰውነታቸውን መደበኛውን 37 ሴንቲግሬድ የሙቀት መጠን ለመቆጣጠር እንደሚያስቸግር ተነግሯል።
እንደ ቦስተን ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ከሆነ ሰውች እየደከሙ በሄዱ ቁጥር የአዕምሯቸው ሙቀት እየጨመረ ይሄዳል።
ስለዚህ ሰውነታችን ከመጠን በላይ እየሞቀ እና እየጋለ ከሄደ ተጨማሪ አእንቅልፍ እንደሚያስፍገን ምልክት ነው ብለዋል ተመራማሪዎቹ።
በተጨማሪም የእነቅልፍ እጦት የውሳኔ አሰጣታችን ላይ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል የሚጠቁሙት ባለሙያዎቹ፤ ስለዚህም አንድ ሰው በአማካኝ በቀን እስከ 8 ሰዓት መተኛት እንዳበትም ይመክራሉ።