በየቀኑ በርካታ ሰው የሚሞትባቸው የአለም ሀገራት
በምድር ላይ በተለያዩ ምክንያቶች በየቀኑ ከ170 ሺህ በላይ፤ በየሰአቱ ደግሞ ከ7 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወት ያልፋል
ቻይና በርካታ ሞት ከሚከሰትባቸው ሀገራት ተርታ በቀዳሚነት ትገኛለች
ውልደት እና ሞት የሰው ልጅ የህይወት ኡደት መገለጫዎች ናቸው፡፡
ሞት በሀይማኖት እና በሳይንስ የተለያዩ ፍቺዎች አሉት፤ ሀይማኖቱ ረጂምም ሆነ አጭር እድሜ ሰዎች በፈጣሪ የተሰጣቸውን ጊዜ አጠናቀው ወደ ቀጣዩ ሕይወት የሚሸጋገሩበት እንደሆነ ያስተምራል፡፡
ሳይንሱ በበኩሉ የሰው ልጅ የምድር ቆይታ እንደሚኖርበት አካባቢ ፣ እንደሚከተለው የህይወት ዘየ እና በኢኮኖሚ ሁኔታው የሚወሰን እንደሆነ ይናግራል፡፡
በሁለቱም መንገድ ብንጓዝ ግን ምክንያቱ ቢለያይም ሰው ሟች ፍጡር መሆኑን በማያሻማ መልኩ እናገኛለን፡፡
በአለም ላይ አይነቱ በተለያየ ሁኔታ የሰው ልጅ በየደቂቃው የሰው ልጅ ህይወት ይጠፋል፡፡
የአለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በተፈጥሯዊ ወይም በበሽታ ከሚጠፋው የሰው ህይወት ጋር በአደጋ፣ በጦርነት እና በሰው ሰራሽ ምክንያቶች የሚሞተው የሰው ልጅ ቁጥር እየተስተካከለ ይገኛል፡፡
ለዚህ ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥ ፣ የተፈጥሮ አደጋ ፣ ሽብርተኝነት እና ጦርነቶች መበራከታቸው ዋነኛ ምክንያት ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡
ወርልድ ፖፕሌሽን ያወጣው መረጃ በ2024 በየቀኑ 170 ሺህ 791 በየሰአቱ 7116 ሰዎች በተለያዩ ምክንያት እንደሚሞቱ ያመላክታል፡፡
በየአመቱ 56 ሚሊየን ሰዎች ምድርን ሲሰናበቱ በየወሩ 4.6 ሚሊየን ሞት ይመዘገባል፡፡
ቻይና በቀን በርካታ ሞት ከሚከሰትባቸው ሀገራት መካከል በቀዳሚነት ትገኛለች፡፡
በሀገሪቱ በቀን 31 ሺህ 974 ሰዎች ሲሞቱ 26 ሺህ 166 ሞት የሚከሰትባት ህንድ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡
በደረጃ ረድፉ 14ተኛ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ በየሰአቱ 89 በ24 ሰአት ውስጥ ደግሞ 2126 ሞት እንደሚመዘገብባት መረጃው ያመላክታል፡፡