ሱዳናውያን አዲስ የፖለቲካ ሽግግር ለመጀመር ያስችላል የተባውን የስምምነት ማዕቀፍ ተፈራረሙ
ስምምነቱ ሱዳን ምርጫ እስክታደርግ ድረስ ለሁለት አመታት በሲቪል እንድትመራ የሚያደርግ ነው ተብሏል
ስምምቱ የቀድሞ መሪ ኦማር አልበሽር ታማኝ ከሆኑ ጸረ-ወታደራዊ ተቃዋሚ ቡድኖች ተቃውሞ ገጥሞታል
የሱዳን የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ኃይሎች በሀገሪቱ አዲስ የፖለቲካ ሽግግር ለመጀመር ያስችላል የተባውን የስምምነት ማዕቀፍ የተፈራረሙ፡፡
በካርቱም በሚገኘው የሪፐብሊካኑ ቤተ መንግስት የተፈረመው ስምምነት በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ተዘፍቃ ለምትገኘው ምስራቅ አፍራካዊቷ ሀገር መፍትሄ ይዞ ሊመጣ ይችላል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
ስምምነቱ ሱዳን ምርጫ እስክታደርግ ድረስ ለሁለት አመታት በሲቪል እንድትመራ የሚያደርግ ነው ተብሏል፡፡
የመጀመሪያው ስምምነት የወታደራዊውን ኃይል በጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ የጸጥታ እና የመከላከያ ምክር ቤት ላይ ያለውን ሚና የሚገድብ ቢሆንም የሽግግር ፍትህ እና የጸጥታ ዘርፍ ማሻሻያዎችን ጨምሮ አሳሳቢ ጉዳዮችን ለቀጣይ ንግግሮች ትቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ስምምነቱ በ2019 ከስልጣን የተወገዱቱን የቀድሞ መሪ ኦማር አልበሽር ታማኝ ከሆኑ ጸረ-ወታደራዊ ተቃዋሚ ቡድኖች እና እስላማዊ ቡድኖች ተቃውሞ ገጥሞታል።
የሱዳን ኮንግርንስ ፓርቲ፣ የሱዳን የባለሙያዎች ማህበር፣ የኮሚዩኒስት ፓርቲ እና አነስተኛ ተቀባይነት ያላቸው ፓርቲዎች ስምምነቱ ከተቃወሙት መካከል ናቸው፡፡
በፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግስት የፊርማ ስነ-ስርአት ከመደረጉ በፊት በዋና ከተማይቱ ካርቱም ቢያንስ በሁለት አካባቢዎች ተቃውሞ መቀስቀሱን የዓይን እማኝ ለሮይተርስ ተናግሯል።
የታሰሩ አባላቶቻችን ሳይፈቱ የስምምነት ማዕቀፉን መፈረም የለበትም የሚሉ ድምጾች መሰማታቸውንም ጭምር ተገልጿል፡፡
ሱዳን በመምራት ላይ የሚገኘው ወታደራዊ መንግስት ከባለፈው አመት መፈንቅለ መንግስት በኋላ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳይሾም በመቆየቱ በወታደራዊ ፣ የነጻነት እና የለውጥ ሃይሎች ጥምረት (ኤፍኤፍሲ) መካከል የነበረውን የስልጣን ክፍፍል ኢንዲቆም አድርጎታል።
መፈንቅለ መንግስቱን ተከትሎ የተፈጠረው የህዝብ የተቃውሞ ማእበል ምክንያት ሀገሪቱ ቀደም ሲል ታገኝ የነበረውን በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር የዓለም አቀፍ የገንዘብ ርዳታ እንዲታገድ በማድረጉ የኢኮኖሚ ቀውስ እየተባባሰ መምጣቱም ይታወቃል፡፡
እናም አሁን የተፈረመው ስምምነት በሱዳን ላይ አዲስ ምእራፍ ሊከፍት እንደሚችል ታምኖበታል፡፡
በፊርማው ስነ-ስርአት ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረት እና የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) ተወካዮች ተገኝተዋል።