ትራምፕ እና ሃሪስ አብዛኛውን የምርጫ ቅስቀሳቸውን በነዚህ ግዛቶች ላይ ሲያደርጉ ሰንብተዋል
አሜሪካ 47ኛ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫዋን ዛሬ በይፋ ትጀምራለች።
ከ78 ሚሊየን በላይ ሰዎች አስቀድመው በኢሜልና በፖስታ ድምጽ በሰጡበት ምርጫ ከ160 ሚሊየን በላይ ሰዎች ቀጣይ መሪያቸውን ይመርጣሉ ተብሎ ይጠበቃልል።
የረጅም ጊዜ የምርጫ ታሪክ ባላት ሀገር የምርጫው ውጤት የሚወሰነው ግን እያንዳንዱ ዜጋ በሚሰጠው ድምጽ ብዛት አይደለም።
ከ50ዎቹ ግዛቶች ውስጥ በሰባቱ የሚመዘገበው ውጤት ነው ውጤቱን የሚወስነው። በ43ቱ ግዛቶች የሚመዘገበው ውጤት አስቀድሞ የሚገመት በመሆኑ።
ፔንሲልቫኒያን ጨምሮ ሰባቱ ግዛቶች ዴሞክራቶች እና ከሪፐብሊካኖች ከፍተኛ ፉክክር ያደርጉባቸዋል።
በመሆኑም የ330 ሚሊየን ህዝብ ባለቤቷ ሀገር ቀጣይ መሪ በሰባቱ ግዛቶች በሚሰጠው ድምጽ ይወሰናል።
ውስብስቡ የአሜሪካ ምርጫና የወኪል መራጮች ድርሻ
የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በየግዛቱ በተመረጡ ወኪል መራጮች አማካኝነት ነው የሚካሄደው።
እያንዳንዱ ግዛት በህዝብ ብዛቱ ልክ ወኪል መራጭ ይኖረዋል፤ መራጮችም የሚፈልጉትን እጩ ፕሬዝዳንት መምረጣቸውን የሚያሳይ ሰነድ በተዘጋጀላቸው የድምጽ መስጫ ቦታ የሚመርጡ ሲሆን የመራጮችን ፍላጎት በማየት ወኪል መራጮች ደግሞ ፕሬዝዳንቱን በቀጥታ ይመርጣሉ፡፡
50ዎቹ ግዛቶች በአጠቃላይ 538 ወኪል መራጮች ያሏቸው ሲሆን፥ እጩዎች ምርጫውን ለማሸነፍ በትንሹ 270 የወኪል መራጮችን ድምጽ ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡
እጩ ተፎካካሪዎቹ የወኪል መራጮቹን እኩል 269 ድምጽ ካገኙ የአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት እያንዳንዱ ግዛት አንድ ተወካዩ ድምጽ እንዲሰጥበት በማድረግ አሸናፊውን ይመርጣል።
በ43ቱ የአሜሪካ ግዛቶች ከዚህ ቀደም የነበሩት ውጤቶች የሚቀጥሉ ከሆነ ካማላ ሃሪስ 226 ፤ ዶላንድ ትራምፕ ደግሞ 219 የወኪል መራጮች ድምጽን ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አሁን ተጠባቂው በሰባቱ ግዛቶች የሚገኙ 93 ድምጾችን ለማግኘት የሚያደርጉት ፉክክር ነው።
የምርጫውን ውጤት የሚወስኑት የትኞቹ ግዛቶች ናቸው?
ሃሪስን አልያም ትራምፕን ወደ ነጩ ቤተመንግስት ለማስገባት ሚቺጋን፣ ፔንሲልቫኒያ፣ ዊስኮንሲን፣ አሪዞና፣ ጆርጂያ፣ ኔቫዳ እና ኖርዝ ካሮሊና ቁልፉን በእጃቸው ይዘዋል።
ሚቺጋን፣ ፔንሲልቫኒያ እና ዊስኮንሲን ሰማያዊ (ዴሞክራት) ነበሩ። ትራምፕ በ2016 ሲያሸንፉ ግን ሶስቱም ግዛቶች ቀይ (ሪፐብሊካን) መርጠዋል።
ከአራት አመት በኋላ ጆ ባይደን ሲያሸንፉ ሂላሪ ክሊንተን በትራምፕ የተቀሙትን የሚቺጋን፣ ዊስኮንሲን እና ፔንሲልቫኒያን ድምጽ ማግኘት ነበረባቸው። ሪፐብሊካኖች ደጋግመው ባሸነፉባቸው ጆርጂያ እና አሪዞናም ያልተጠበቀ ድል ማስመዝገባቸው ይታወሳል።
በአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ፉክክር ፔንሲልቫኒያ ትልቅ ትኩረት ይሰጣታል። 19 ወኪል መራጮች ያሉባት ግዛት የምርጫውን ውጤት ለመወሰን ትልቅ ድርሻ አላት። እንደ ካሊፎርኒያ እና ቴክሳስ ያሉ ግዛቶች ከፔንሲልቫኒያ የላቀ የወኪል መራጮች ቢኖራቸውም የሚሰጡት ድምጽ ሁሌም ተጠባቂ ነው።
ትራምፕ የግድያ ሙከራ በተደረገባቸው ፔንሲልቫኒያ በተደጋጋሚ የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ መክረማቸውም ለዚያ ነው።
ሃሪስ በፔንሲልቫኒያ ከተሸነፉ በኖርዝ ካሮሊና አልያም ጆርጂያ ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል።
በአንጻሩ ትራምፕ በፔንሲልቫኒያ ከተሸነፉ ዳግም ወደ ዋይትሃውስ ለመዝለቅ ዊስኮንሲን አልያም ሚቺጋን ላይ ሊመረጡ ይገባቸዋል።
የሃሪስም ሆነ የትራምፕ የቅስቀሳ ቡድን ከሁሉም ግዛቶች በበለጠ ለፔንሲልቫኒያ ትኩረት መስጠታቸውን ለማስታወቂያ ያወጡት ወጪ አመላካች ነው። የቅስቀሳ ቡድኖቹ በቴሌቪዥን እና በሬዲዮ ለሚተላለፉ ማስታወቂያዎች 280 ሚሊየን ዶላር ወጪ አድርገዋል።
በሰባቱ ግዛቶች ከሁለቱም ፓርቲዎች ገለልተኛ የሆኑ ዜጎች የሚሰጡት ድምጽ ከ43ቱ ተገማች ግዛቶች ይልቅ ተጠባቂ ሆኗል።